የንጹሕ መጠጥ ውሃ ስርጭት ፍትሐዊ አለመሆን ለኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዳት እየዳረገን ነው የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች

የንጹሕ መጠጥ ውሃ ስርጭት ፍትሐዊ አለመሆን ለኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዳት እየዳረገን ነው የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች

ሀዋሳ፡ ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የንጹሕ መጠጥ ውሃ ስርጭት ፍትሐዊ አለመሆን ለኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዳት እየዳረገን ነው ሲሉ በሆሳዕና ከተማ የአራዳ ቀበሌ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የከተማ አስተዳደሩ ውሃ አገልግሎት ጽ/ቤት በበኩሉ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

አቶ አበራ ለሬቦ እና ወንደሰን ደምሴ በቀበሌው በተለምዶ ሌባሻ ሊዝ ሰፈር በሚባል መንደር የሚኖሩ ሲሆን በ2007 ዓ/ም በወጣው ሊዝ ጨረታ ካሸነፉ በኋላ ንጹሕ የመጠጥ ውሃን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በህብረተሰብ ተሳትፎ ማሟላት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ንጹሕ የመጠጥ ውኃው ከወራት በኋላ በሀይል ማነስ ምክንያት አገልግሎት መስጠት እንዳቆመ ገልጸው፥ ከዚህ የተነሳ ለብዙ ጊዜያት ንጹሕ የመጠጥ ውሃ በማጣት በኑሯቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ በዚህ ዓመት አጋማሽ አካባቢ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ከውሃ አገልግሎት ጽ/ቤቱ ጋር በመናበብ አዲስ መስመር እንዲዘረጋ በማድረግ የተወሰነ መጠቀማቸውን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ድረስ በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት መቸገራቸውን ነው የተናገሩት።

በቀበሌው በተለምዶ ሸውል ሜዳ በሚባልበት መንደር የሚኖሩ አንዳንድ ነዋሪዎች በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ከአራዳ ቀበሌ አልፎ ለሌሎች ቀበሌያት የሚበቃ የውሃ ፕሮጀክት ገንብቶ በዚህ ዓመት አጋማሽ አካባቢ አገልግሎት እንዲሰጥ ቢያደርግም ትክክለኛ ተራ አውጥቶ ከማሰራጨት አንጻር ጉድለት መኖሩን ጠቁመዋል።

በዚህም ንጹሕ የመጠጥ ውሃ በማጣት ለኢኮኖሚያዊ እና ለማሕበራዊ ችግር እየተደረጉ እንደሆነ አንስተዋል።

ችግሩ ከሌሎች ቀበሌያት አንጻር በአራዳ የጎላ ቢሆንም በአብዛኛዎቹ ቀበሌያት እንደምስተዋል የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ በመርሀ ግብሩ መሠረት ተራ ጠብቆ ያለ መልቀቅ ለችግሩ መንስኤ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የሚመለከታቸው አካላት በቂ የውሃ ኃይል እያለ እና ፍትሐዊ የውሃ ስርጭት ባለመኖሩ ምክንያት የሚደርሰውን መጉላላትና እንግልት መቅረፍ አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ውሃ አገልግሎት ጽ/ቤት የአራዳ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ታጋይ አባመጫ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የነዋሪውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርጸው በመንቀሳቀስ ተደራሽነቱን በዕጥፍ ማሳደግ እንደቻለ ተናግረዋል።

ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በከተማው ከሚገኙ ስድስት ቀበሌያት ውስጥ ለአራቱ አገልግሎት እንደሚሰጥ የጠቆሙት አስተባባሪው የቀበሌያቱ እርካታ 75 በመቶ እንደሆነ የዳሰሰ ጥናት ያመለክታል ብለዋል።

የመሬት አቀማመጡ ምቹ አለመሆን፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የኮሪደር ልማት እና የውሃ መስመሮች ተደጋጋሚ ብልሽት መጋጠም ለችግሩ መንስኤ እንደሆነ የገለጹት አስተባባሪው ሕብረተሰቡ እንደ ጉድለት ያነሳቸውን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን