ማህበራት የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የስራ ዕድል ፈጠራን ተግባራዊ በማድረግ ከምስለ ምርት ለገበያና ችግር ፈቺ ምርት ወደ ማምረት መሸጋገር እዳለባቸው ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የስራ ዕድል ፈጠራን በመተግበር ማህበራት ከምስለ ምርት ለገበያና ችግር ፈቺ ምርት ወደ ማምረት መሸጋገር እዳለባቸው የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ::
የስራ ክህሎት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ የተመራ ቡድን በክህሎት ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በተቋም ግንባታ ዙርያ በጉራጌ ዞን ቸሀ ወረዳና ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የመስክ ምልከታ አድርጓል።
በመስክ ምልከታው የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት በዘርፉ የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተለይም የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የስራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴን በመገምገም ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ማህበራት ከምስለ ምርት ለገበያና ችግር ፈቺ ምርት ወደ ማምረት መሸጋገር እዳለባቸው ገልፀዋል::
ኢንተርፕራይዞች እስከ ተጠቃሚው የሚደርሱበት የእሴት ሰንሰለት መሰረት ያደረገ ስራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው፥ ተገቢውን ድጋፍ ቢያገኙ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የበኩላቸውን ሚና እንደሚያበርክቱ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል::
የአንድ ማዕከል ተቋማት ስራ ፈላጊ ዜጎች በስልጠና፣ በብቃት ማረጋገጫና በሌሎችም እንዲበቁና በስራ ስምሪትና በኢኮኖሚያዊ እድገት ከራሳቸው አልፈው ለሀገር የበኩላቸውን የሚያበረክቱ ማዕከላት መሆቸውን አስረድተዋል::
በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው የገለፁት አቶ ሰለሞን፥ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ካሉት በመማር፣ የግሉን ዘርፍ በማጠናከርና የስራ ዕድል በመፍጠር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የበኩላቸውን እንዲያበርክቱ ማስቻል እንደሚገባ አስገንዝበዋል::
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው፥ መንግስት የመሬት አቅርቦት በማመቻቸት ማህበራት በግብርና በመሰማራት በመስኖ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ከራሳቸዉ አልፈው ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ጠቁመው፥ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እየተሸጋገሩ የስራ እድል በመፍጠርና በኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል::
ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ከተቻለ በስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል ተናግረዋል::
በክልሉ ባለፉት 10 ወራት ለ333ሺ 118 ዜጎች ቋሚና የውጭ ሀገር የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልፀው እስከ 2019 ዓ/ም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች በግብርና በአገልግሎት በማኑፋክቸሪንግና በሌሎችም ዘርፎች የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አክለዋል::
የጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙራድ ያሲን እንደተናገሩት ከጅምር እስከ ሽግግር ድጋፍ በማድረግ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር ተችሏል::
በዞኑ 249 ኢንተርፕራይዞች መመዝገባቸውን ጠቁመው በዞኑ በሰብልና በከብት እርባታ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች በአመት ሁለቴና ሶስቴ በማምረትና ሌሎችም በተሰማሩባቸው ዘርፎች ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል::
በዞኑ ቸሀ ወረዳና ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በመስኖ፣ በአትክልት ልማት፣ በከብት እርባታና በጥምር ግብርና ከተሰማሩ አብድልኑር መሀመድ፣ መሪሁን ሽኩርና ሚነወር ይብጌታ እንደገለፁት በመንግሥት የተመቻቸላቸውን የብድርና የመስሪያ ቦታ በመጠቀም በተገቢው መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል ::
ውጤታቸውን በማየት ሌሎችም ወደ ስራ እየገቡ መሆኑን ጠቁመው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መሆኑን ተናግረዋል::
በጉብኝቱ በዞኑ ቸሀ ወረዳና ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በጥምር ግብርና በአትክልትና ፍራፍሬ በእርባታ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የአንድ ማእከል አገልግሎትና በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ከፕሮጀክቶች ጋር በመቀናጀት እየሰጠ ያለው ክህሎት ነክ ስልጠና እና የውስጥ ገቢን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተመልክተዋል።
ዘጋቢ: ሄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ
“የብልጽግና ጉዞአችንና የንግዱ ማህበረሰብ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ክልላዊ የንግዱ ማሕበረሰብ ማጠቃለያ የውይይት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው
በዞኑ ኩረጃን የሚፀየፍ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ