ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ሰላም እና ተጠቃሚነት ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ሰላም እና ተጠቃሚነት ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጋሞ ዞን የተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ሰላም እና ተጠቃሚነት ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።
‎
‎”ለተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት እና ባህል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና” በሚል ርእስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዞናዊ የውይይት መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ተካሂዷል።
‎
የመድረኩ አላማ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል እና በጋራ ሃገራዊ ለውጡ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ተረድተው በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በመተማመን ተቀራርበው እንዲሰሩ ማስቻል መሆኑ ተመላክቷል።
‎
‎መንግስትን በመወከል በመድረኩ የተገኙት የጋሞ ዞን ህዝብ ምክርቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሪት አለሚቱ ዮሴፍ በአገሪቱ በ7 አመታት ውስጥ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በውል ተረድተው ጤናማ የሆነ ፉክክር ሊያካሂዱ እንደሚገባ ተናግረዋል።
‎
‎በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በቀረበው ሰነድ ሃገራዊ ለውጡን ያጋጠሙ ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች በዝርዝር የቀረበ ሲሆን የጽንፈኝነት፤ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭት ከአስተሳሳሪ ትርክት ይልቅ በነጠላ ትርክት ላይ ማተኮር በተግዳሮትነት ተነስቷል።
‎
‎የኢሶዴፓ ፓርቲ ተወካይ አቶ ወንድሙ ኡቶ እንደተናገሩት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሃይል አማራጭ ከመጠቀም ወጥተው ለወከላቸው ህዝብ ተጠቃሚነት አበክረው መስራት አለባቸው።
‎
‎ህብር ኢትዮጵያ ፖርቲን በመወከል የተገኙት አቶ አለማየሁ ገ/መድህን ደግሞ ገዢው መንግስት ከተፎካካሪ ፖርቲዎች ጋር ለመስራት ፍላጎት ማሳየት ያለበት ምርጫ ሲቃረብ ብቻ መሆን እንደሌለበት ጠቁመው፥ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት መንግስት በቁርጠኝነት መስራት አለበትም ሲሉ አፅንኦት አሳስበዋል።
‎
‎የመኢኣድ ፓርቲን ወክለው የተገኙት አቶ ወንዱ ወንዳፍራሽ የዞኑ የፖለቲካ ፓርቲ ተወያይቶ በስራ እድል ፈጠራና በኑሮ ውድነት ላይ ለውጥ ማምጣት እንዲችል በጋራ መስራት ይጠበቃል።

‎
ከእናት ፓርቲ የተገኙት የጋሞ ዞን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስ ፋንታ በውይይት መድረኩ መዘጋጀት የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸው በሃገሪቱ አንጻራዊ የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱን መስክረዋል።
‎
የእናት ፓርቲ ተወካይ ‎ወ/ሮ የትምወርቅ ነጋሽ በሃገራዊ ለውጡ ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር የቀረበው ሰነድ ይዘትን አወድሰው ፤ሃገራዊ ሰላምን ለማስጠበቅ ብሎም የኑሮ ውድነትን በመቆጣጠር በኩል መንግስት በትኩረት መስራት ያሻዋል ብለዋል።

ዘጋቢ: አሰግድ ተረፈ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን