የሀለባ ዞን ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢልዮን 293 ሚልዮን ብር ባለይ በጀት አጸደቀ

የሀለባ ዞን ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ከ3 ቢልዮን 293 ሚልዮን ብር ባለይ በጀት አጸደቀ

ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው የምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 11ኛ ዓመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቋል።

የዞኑ ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ረውዳ ሐጅ ዘይኔ እንደገለፁት ምክርቤቶች በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና በመንግሥት አሠራር የህዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ በህብረተሰቡ መብትና ነፃነት ላይ አዎንታዊ ለውጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አመላክተዋል።

በሀገራችን እየታዩ የመጡ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል የሁሉንም የጋራ ርብርብ ይሻል ያሉት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ፥ የኢኮኖሚያችን ጀርባ አጥንት የሆነው የግብርና ዘርፍ በሀገርቱ እንዲሁም በዞኑ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀው፥ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በዞኑ ከሰላምና ፀጥታ አንፃር የመጡ ጅምር ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ በተለያዩ ዘርፎች በተሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉ የሚበረታታ ቢሆንም፥ ከህብረተሰቡ ፍላጎትና ካለው ዞናዊ አቅም አንፃር በቀጣይ ውስንነቶችን በመለየት ብዙ ስራ መስራትን የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል።

የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለይቶ ከመፍታት አንፃር ያሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባ ወይዘሮ ረውዳ አንስተዋል።

የሀለባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፥ በቀጣዩ በጀት ዓመት የዞኑን ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ በከተማውና በገጠር አካባቢዎች የስራ ዕድል ፈጠራን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በ2019 በጀት ዓመት በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤናና ሌሎችም ዘርፎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሻሻል በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ምክርቤቱ ለ2019 በጀት ዓመት ማስፈጸሚያ 3 ቢልዮን 293 ሚልዮን 518 ሺህ 873 ብር ረቂቅ በጀት ማጽደቁም ተመላክቷል።

የዞኑ ፍርድ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እና 2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ በጉባኤውም በተለያዩ የመሠረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው በባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በመጨረሻም በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መስሪያ ቤቶች የዕውቅና ሰርተፍኬትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ: ሙዘይን ሰኒ – ከሆሳዕና ጣቢያችን