የጤና ተግባራት በኃላፊነት እና በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የይርጋጨፌ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጥላሁን ገለጹ።
የፒ.ኤስ.አይ ኢትዮጵያ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከይርጋጨፌ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር “የማህበረሰብ ተሳትፎ ለጤና” በሚል መሪ ሀሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካህዷል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የይርጋጨፌ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጥላሁን፥ የጤና ተግባር ሁሉም ሴክተሮች በኃላፊነት እና በቅንጅት የሚሠሩት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ እስከ ድህረ ወሊድ ያለውን ጊዜ ክትትል እንዲያደርጉ በስፋት መሰራት እንዳለበት አቶ ተካልኝ አንስተዋል።
አምራች ዜጋን ለማፍራት የህጻናት መቀንጨር ትልቅ ማነቆ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፥ ለብሩህ አእምሮ እና ዕድገት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለባቸው ብለዋል።
በፒ.ኤስ.አይ ኢትዮጵያ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተባባሪ ዶ/ር ታምራት ተስፋዬ፣ ድርጅቱ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አንስተው፥ በእናቶች እና ህጻናት ጤና እና በስርዓተ ምግብ ፕሮግራም ለመዘርጋት እና ማስተዋወቂያ የውይይት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
በወረዳው ለሁለት ዓመታት እንደሚቆይ ያነሱት አስተባባሪው፥ በቆይታ ጊዜያቸውም በስርዓተ ምግብ፣ በእናቶች እና ህጻናት ጤናና ሌሎች የጤና አመለካከቶች ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ በቀለ በበኩላቸው፣ የማህበረሰብ ጤና ልማትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ድርጅቱ የማህበረሰቡን የጤና ችግር ለመቅረፍ ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ ዉይይቱ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ አሀዱ አሸናፊ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ጥራቱ የተጠበቀ ከ500 ቶን በላይ እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲሱ የካቢኔ ስብጥር ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን በተግባር ያሳየ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
ዕጩ የካቢኔ አባላት ከወትሮ በተለየ መንገድ ባለዕዳና ከፍተኛ አደራ የተጣለባቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ ማሳሰብ እወዳለሁ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)