መምህር ትውልድ በመቅረፅና በመገንባት ለሀገር እድገትና ብልጽግና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለፀ
በጂንካ ዩኒቨርሲቲ “ትውልድ በመምህር ይቀረፃል፤ ሀገር በትምህርት ትበለፅጋለች” በሚል መሪ ቃል ከአጠቃላይ መምህራን ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ ይትባረክ፤ መምህር ትውልድ በመቅረፅና በመገንባት ለሀገር እድገትና ብልጽግና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀው በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር ካላቸው አበርክቶ አንፃር መምህራን በእውቀትና በክህሎት እራሳቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፤ መምህራን ለሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በመንግሥት በኩል ተወስደው መሰራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በግልፅ ውይይት የተደረገበት መድረክ በመሆኑ ለሰላም ግንባታም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
በሀገራዊ መድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፤ ለተያዘው ለብልጽግና ጉዞ መምህራን ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልፀው በተለይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚሳተፉ የትምህርት ስብራትን በመጠገን ጥራቱ ላይ ለዉጥ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ መምህራን በሰጡት አስተያየት መንግስት በትምህርትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የሚሰራቸው ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለው የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ከመንግስት ጎን በመሆን ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡና መንግስትም የሚነሱ ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንደአለበት አንስተዋል።
ዘጋቢ፡ ዳኛቸው ደሴ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የግል እና የጋራ መጸዳጃ ቤቶችን በተገቢው በመጠቀም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስገነዘበ
12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በተቋማት የድርጊት መርሐ-ግብርና በፀደቀላቸው በጀት መሠረት ማሰራጨቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ አስተዳደር እየተገነባ የሚገኘውን ብሉ ኤለፋንት ፋይበር ቦርድ ካምፓኒ ጎበኙ