በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች የማህበረሰቡን ችግር በመቅረፍ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው ተጠቆመ
5ኛው ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በእርሻና ተፈጥሮ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በጤና ሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ፣ ማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ከሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል።
መምህር መላኩ ሀይሌ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ድግሪያቸውን እያጠኑ ሲሆን በአካባቢው ብቻ ስለሚገኘው የጦጣ ዝሪያ ላይ ያደረጉትን የጥናት ውጤት ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ዝርያው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ መሆኑን ያመላከቱት አጥኚው፤ ይህን የተለየ የጦጣ ዝርያ መጠበቅ ከተቻለ በቱሪዝም ዘርፍ ለአካባቢው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል።
ሌላው ተመራማሪ መ/ር መልካሙ በቀለ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሲሆኑ ከኤሌክትሪክ ሀይል ባለፈ ታዳሽ ሀይል አጠቃቀም ላይ ትኩረት ያደረገ ጽሁፍ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ በቂ ሀብት እንዳላት ያመላከቱት ተመራማሪ እና መ/ር መልካሙ፤ በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን የለየ ጥናት ያቀረቡ ሲሆን ለተግባራዊነቱ ከዘርፉ ባለሙያዎች እና ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይሁን ከፍተኛ ምርት በመስጠት ከሚታወቁ የአዝርዕት ምርቶች መካከል ቀዳሚ ስለመሆኑ የሚነገርለት የበቆሎ ዘር ላይ ጥናት ያቀረቡት ደግሞ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ እና መ/ር አለሙ ዱጋሳ ናቸው።
እንደ አጥኚው ገለጻ የአካባቢው አርሶ አደሮች የሚጠቀሙት የበቆሎ ዝርያ በግብርና ምርምር ያልተረጋገጡ ስለመሆናቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ ከግብርና ምርምር ተቋማት የተገኙ ምርጥ ዝርያዎችን ከመጠቀም ይልቅ የተገኘውን ከገበያ እንደሚገዙ አመላክተው ይህም ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ለዚህም ምርጥ ዘር የሚያቀርቡ የግብና ምርምር ተቋማት አለመኖር በምክንያትነት ያቀረቡት ተመራማሪው፤ መፍትሔ ያሏቸውንም ምክረ ሀሳቦችም ለባለድርሻ አካላት አመላክተዋል።
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማዕድን ሀብት መጠቀም የሚቻልበት መንገድ፣ ባህላዊ መድኃኒቶችን ለተሻለ ጤና እንዲሁም የህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች በሚመለከት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።
በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎችም ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ጥናት እና ምርምሮች የማህበረሰቡን ችግር በመቅረፍ እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው በኮንፍረንሱ ተገልጿል።
በምርምር ኮንፍራንሱ የግብርና ምርምር ተቋማት ተወካዮች፣ ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ለኮንፍረንሱ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እና ግለሰቦች የምስክር ወረቀት እንደሚሰጥ ከወጣው መርሃ-ግብር መረዳት ተችሏል።
ሁለት ቀናት በተካሄደው የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ከ20 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል።
ዘጋቢ፡ ድንቃየሁ ዮሐንስ – ከቦንጋ ያቢያችን
ፎቶ፡ በረከት ገብረኪዳን – ከቦንጋ ያቢያችን
More Stories
የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የኡዱሂያ የዕርድ ስርዓት….የአብሮነት ነፀብራቅ
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ