የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና ጉልህ አበርክቶ አለው – ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ

የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና ጉልህ አበርክቶ አለው – ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና ጉልህ አበርክቶ አለው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ገለፁ።

“ትውልድ በመምህር ይቀረፃል ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል!” በሚል መሪ ቃል ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር የጋራ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

በመድረኩ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳዊት ሃዬሶ ምሁራን በሀገሪቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምርምሮችን በማድረግ ለዜጎች ሁለንተናዊ ለውጥ በርካታ ስራዎችን የመስራት ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ አንድነትን የሚነጣጥሉ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመዋጋት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ የጋራ ገዢ ትርክቶችን ከማጎልበት ረገድ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ የምሁራን ሚና ተኪ የሌለው መሆኑን አመላክተዋል።

በተለያዩ ዘርፎች ከሴቶች እኩል ተጠቃሚነት አንፃር አንፃራዊ ለውጦች ቢኖሩም በሚፈለገው ልክ ያለመሆኑን ጠቁመው ቀጣይ ለዘላቂ ለውጥ ይሰራል ብለዋል።

ዶክተር ዲላሞ አክለውም ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አፍራሽ አመለካከቶችን ብሎም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚከፋፍሉ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል የወል ትርክቶችን በማንገብ ለሀገሪቱና ዜጎቿ ሁለንተናዊ ልማትና ተጠቃሚነት ሁሉም በቅንጅት መስራት አማራጭ የሌለው የመፍትሔ አቅጣጫ መሆኑን አመላክተዋል።

በዚህ ወቅት መንግስት የዜጎችን ዘላቂ ሠላምና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው ሁሉም ለጋራ ሀገሩ ለውጥ በሚደረጉ ጥረቶች አጋር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ማቴዎስ አኒዮ የዞኑን ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማየት መቻሉን ጠቁመው በቀጣይም የንፁህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ጨምሮ ከህብረተሰቡ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የዞኑ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በበኩላቸው መንግስት የዜጎችን ሠላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን በመጠቆም ለትምህርት ጥራት ተግዳሮቶች በሚሆኑ ጉዳዮችና ተዛማጅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባለድርሻ አካላት የላቀ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የሀገር እድገት መሰረቱ ትምህርት ከመሆንም በላይ መምህርነት የትውልድ ኃላፊነት እንደመሆኑ ለዘርፉ ውጤታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በመጠቆም።

በመድረኩም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ሠላምና እድገት ከምሁራኑ በሚጠበቁ ሚናዎች ላይ በአጽንኦት የተመከረ ሲሆን ከምሁራኑ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን