ከ19ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች አገር አቀፍ ፈተና ይወስዳሉ – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ ዓመት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና አጠቃላይ ከሚፈተኑ19ሺህ በላይ ተማሪዎች ዉስጥ ከ2ሺህ 600 በላይ ተማሪዎች በኦንላይን ፈተና እንደሚፈተኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነሜ እንደገለፁት በዘንድሮ ዓመት በሚሰጠዉ የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ተማሪዎችን ዉጤታማ ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
አምና በነበረዉ የአገር አቀፍ 12ኛ ክፍል ፈተና በክልሉ ሰፊ ቁጥር ያላቸዉ ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ወደ ዩንቨርሲቲ ያላስገቡ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ደስታ፥ በዘንድሮ አመት ችግሩ ጎልቶ እንዳይታይና ትምህርት ቤቶቹ ዉጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ ኢንሼቲቮች ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎቹን ዉጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያሉትን የትምህርት ይዘቶች በመሸፈንና የልዩ ማጠናከሪያ ትምህርት ፕሮግራም በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ በዘንድሮ አመት በሚሰጠዉ የ12ተኛ ክፍል የአገር አቀፍ ፈተና አጠቃላይ 19ሺህ 127 ተማሪዎች ፈተናዉን እንደሚፈተኑ የገለጹት ዶክተር ደስታ፥ ከእነዚህ ተማሪዎች ዉስጥ 2ሸህ 690 ተማሪዎች የኦንላይን ፈተና እንደሚፈተኑ ገልፀዋል።
የኦንላይን ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎችም በክልሉ ዉስጥ ባሉ አራት ከተማ አስተዳሮች ዉስጥ ባሉት አስራ አንድ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መሆናቸዉን ተናግረዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች በስነ -ልቦና ዝግጁ መሆን እንዳለባቸዉ የጠቆሙት ዶክተር ደስታ ወላጆችም የድርሻቸዉን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡ ቸርነት አባተ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የኡዱሂያ የዕርድ ስርዓት….የአብሮነት ነፀብራቅ
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ