በወረዳው በየደረጃው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወረዳው በየደረጃው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት፣ የሰላም እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በጉራጌ ዞን የአበሽጌ ወረዳ ምክር ቤት ገለፀ፡፡
የወረዳው ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ አመት 38ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአበሽጌ ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ታደሰ ፈቀደ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በወረዳው የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሀር ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፤ በግብርናው ዘርፍ በፀደይ እና በበልግ ወቅት የእርሻ ዝግጅት 59 ሺህ 658 ሄክታር መሬት ላይ በተሰራ ስራ በተለይም በሽምብራ፣ በጥራጥሬ፣ በአገዳ፣ በቅባትና በብርዕ ሰብሎች 3 ሚሊዮን 660 ሺህ 856 ኩንታል ማምረት መቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም አርሶአደሩን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በተደረገ ጥረትም ለ17 ሺህ 780 አርሶ አደሮች ስልጠና መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡
በወረዳው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ምርት ቤት ለቤት ለመሰብሰብ ታቅዶ ሲሰራ መቆየቱን በማንሳት እስካሁን ባለው ሂደትም 7 ሺህ 779 ኩንታል መሰብሰብ መቻሉን ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለፁት።
በትምህርት ለትውልድ ሀብት አሰባሰብ በጥሬ ገንዘብ፣ በጉልበት፤ በቁሳቁስና በአይነት 16 ሚሊዮን 326 ሺህ 475 ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን በመጠቆም በወረዳው በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የመፅሀፍት ህትመት 6 ሚሊየን 450 ሺህ ብር ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የመማር ማስተማር ስርአትን ለማሻሻል የመምህራን ሙያዊ ብቃትን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በወረዳው በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በገቢ አሰባሰብ እና በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች የልማትና መልካም አስተዳደር ዘርፎች ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወን መቻሉን ዋና አስተዳዳሪው በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በመጨረሻም ከምክር ቤቱ አባላት በኩል ከማዳበሪያ ግብአት አቅርቦት ችግር፣ ያልታረሱ መሬቶችን ከማረስ አንፃር፣ ከተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ እና ከወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን ለተነሱ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ፡ ዘይኔ ሁንዲቶ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ82 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ መቆርቆር ቀበሌ ያስገነባው የንጹህ መጠ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የኡዱሂያ የዕርድ ስርዓት….የአብሮነት ነፀብራቅ
በቅርቡ በሚሰጠው የ6ኛ እና የ8ኛ ክልላዊ ፈተና ላይ ከ53 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀርቡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ትምህርት መመሪያ አስታወቀ