ሀዋሳ፣ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ “ትውልድ በመምህር ይቀረጻል ፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል የመምህራን ውይይት እየተካሄደ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ዶክተር ደገለ ኤርገኖ፤ የመድረኩ ዓላማ የመምህራንን ሀሳብ ለማድመጥና እርስ በእርስ መወያየት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ነው ብለዋል።
መንግስት ለሚሰራቸው ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ከምሁራን ለማግኘትና ተግባራዊ ለማድረግ በሀገር-አቀፍ ደረጃ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰመስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ መምህርነት ለሀገር ጠቃሚ ዜጎችን የሚያፈሩበት የተከበረ ሙያ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡ አሁን የደረሰበትን ደረጃና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በሚመለከት ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ አሰባሳቢ ትርክትን ለመፍጠርና ህብረ-ብሔራዊነትን ለማፅናት የመምህራን አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የትምህርት ዘርፍ ሙያዊ ነፃነቱ ተጠብቆ እንዲቀጥልና ሀገርን መምራት የሚችሉ ምሁራንን ለማፍራት እንዲቻል በመንግስት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ነው የተናገሩት።
በትምሀርት ዘርፍ ከተከናወኑ የለውጥ ስራዎች መካከል ሙያዊ ነፃነትን ለማስከበር፣ የፈተና አሰጣጥንና አጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ተጨባጭ ለውጥ መታየት ጀምሯል ነው ያሉት።
የተወዘፉ የትምህርት ዘርፍ ችግሮችን በመለየት ባለፉት ሰባት ዓመታት ለውጥ መታየቱን ገልፀዋል።
በመድረኩ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን እና የቀጣይ ስራ አቅጣጫዎችን የሚመለከት ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ዮሐንስ ክፍሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ ለ9ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን አስመረቀ
ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” – አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ