ሀዋሳ፡ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመገንባት ላይ ያሉ የመስኖ አውታር ዝርጋታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ የመስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል አፈ ጉባኤ የተመራ ልዑክ በክልሉ የተጀመሩ የመስኖ ዝርጋት ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመገንባት ላይ ከሚገኙ የመስኖ ሮጀክቶች አንዱ በጎፋ ዞን ዑባ ደብረ ጸሐይ ወረዳ የሚገኘው የሎማቴ የመስኖ ፕሮጀክት መሆኑ ተመልክቷል።
አርሶ አደር ፖሊሴ ፖኮ እና ስንታየሁ ፍርዴ በሎማቴ ወንዝ ታግዘው በባህላዊ መንገድ በመስኖ እርሻ የሚያለሙ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ክረምት ከበጋ በሚፈሰው በዚሁ ወንዝ ላይ የተጀመረው የመስኖ ዝርጋታ ምርታማነታቸውን እንደምጨምርላቸው ገልጸው የሚታየው የግንባታ መዘግየት ችግር እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የመስኖ ዝርጋታው ሲጠናቀቅ ከ700 ሔክታር በላይ መሬት በማልማት ከ2ሺህ 800 በላይ አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተብራርቷል።
በ267 ሚሊዮን 551 ሺህ 661 ብር በወላይታ ውሃ ሥራዎች ተቋራጭ በመገንባት ላይ ያለው የሎማቴ መስኖ ዝርጋታ በተያዘለት ጊዜ ያልተጠናቀቀው በበጀት እጥረት እና ግንባታ ቁሳቁሶች ዋጋ ንረት መሆኑን የሚናገሩት የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አክልሉ ደቢሳ፥ መንግሥት ተገቢው በጀት የሚመድብ ከሆነ ሥራውን ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት አማካሪ የሳይት ተቆጣጣሪ አቶ ይሁን ዘለቀ በበኩላቸው የመስኖ ዝርጋታው ሊዘገይ የቻለው ወቅታዊ የነዳጅ፣ የግንባታ ቁሳቁሶች የዋጋ ንረት እና በተቋራጩ ድርጅት የአቅም ውስንነት መሆኑን አክለው ለሥራው መሣካት የሁሉም ድጋፍ ይሻል ነው ያሉት።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቁላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሐብቴ በበኩላቸው የመስኖ ዝርጋታ ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማረም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ እና ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲሁ የመስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ የሥራ ሀላፊዎች የግባታ ሂደት ያለበትን ሁኔታ ገምግመው አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገለጹ
የእናቶችንና ጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳደር (ዶ/ር ) እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስረዓት እየተካሄደ ይገኛል