ሀዋሳ፡ ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ሁለንተናዊ ጤና ለሀገር ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል ከጤና ባለሙያዎች ጋር የውይይት መድረክ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ተካሄደ።
በመድረኩ የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሊቃውንት አዛዘ ሰነድ ያቀረቡት ሲሆን በሀገር ደረጃ በፖሊቲካው፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ስራዎች መሰራቱን ጠቁመዋል።
አንዳንድ ባለሙያዎች ሰዓትን አክብሮ አለመስራት፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮች እና ሌሎች ጉድለቶች የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
የጤና ባለሙያዎች በሀገር ግንባታ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር፣ ትውልድን በመልካም ስነ-ምግባር ማነጽ፣ መብትና ግዴታን የሚረዱ ባለሙያዎችን መፍጠር፣ ለሀገር ጥቅም የማይደራደር ትውልድ ማፍራት ቀጣይ የመንግስት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ጤና ባለሙያዎች ደመወዝና የትርፍ ሰዓት ክፍያ ማነስና በአግባቡ አለመከፈል፣ የነፃ ህክምና አገልግሎት አለመኖሩ፣ ለባለሙያዎች ክትባት አለመኖር፣ የደረጃ ዕድገት በአግባቡ አለመሰጠት፣ ዝውውር እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
አክለውም ተሽከርካሪ አለመኖር፣ የመንገድ ችግሮች፣ የኬሚስትሪና ሌሎች የህክምና ማሽኖች እጥረት መኖር፣ በአንዳንድ የጤና ተቋማት የጤናውን ሴክተር ስራዎች በቦርድ አለመገምገም እና ሌሎች በርካታ ችግሮች በጤናው ዘርፍ የሚታይ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ከተሳፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሽያለው እና የዞኑ ጤና ጥበቃ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሊቃውንት አዛዘ የጤና ባለሙያው በሰለጠነው ሙያ መሰረት በችግሮች መካከል ለህብረተሰቡ እየሰጠ ላለው ሙያዊ አገልግሎት አመስግነው የተነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ የሚመለሱ ናቸዉ ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የጤና የልማት ዕቅድና ኢኮኖሚ አስተዳደር ዋና ዳይሬከተር እና የቢሮው ኃላፊ ተወካይ አቶ ተገኝ ጮቴ መንግስት የጤናውን ዘርፍ በጤና ፓሊሲ መሠረትና በአዋጆች ተደግፎ የሚፈፀም መሆኑን ተናግረው አሁን የጤና ባለሙዎች ጥያቄ ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።
በቀጣይ በክልላዊ መድረክ ላይ የሚሳተፉ 22 ተሳታፊዎችን በመምረጥ መድረኩ ተጠናቋል።
ዘጋቢ: ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሳውላ ካምፓስ ለ9ኛ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 121 ተማሪዎችን አስመረቀ
ዲግሪው “ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሀገር ተስፋና የትውልድ ኃላፊነት ነው” – አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር)
በክልሉ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ