በጂንካ ከተማ ከ6 ሺህ ደርዘን በላይ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፋቸው ለስላሳ መጠጦች ተወገዱ

በጂንካ ከተማ ከ6 ሺህ ደርዘን በላይ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፋቸው ለስላሳ መጠጦች ተወገዱ

ሀዋሳ፡ ግንቦት14/2017ዓ.ም (ደሬቴድ) የኣሪ ዞንና ጂንካ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት የጋራ ግብረ-ኃይል በጂንካ ከተማ ከ6ሺህ 2መቶ በላይ ደርዘን የአገልግሎት ጊዜ ያለፋቸው ለስላሳ መጠጦችን አስወገዷ።

ምርቶቹ በከተማ አስተዳደሩ የምስራቅ አፍሪካ ለስላሳ መጠጦች ሼር ካምፓኒ የኮንሶ አከባቢ ወኪል ጂንካ ቅርንጫፍ መጋዝን እንደተገኘ ተመላክቷል።

የምስራቅ አፍርካ ለስላሳ  መጠጦች ሼር ካምፓኒ የጂንካ ወኪል ተወካይ አቶ አዝማች ኦርካይዶ እንደገለፁት በድርጅታቸው ምርቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜ ስያልፋቸው በአቅራቢያ ለሚገኝ ባለስልጣን መሥሪያ ቤት በማሳወቅ ስያስወግዱ እንደነበርና በዚህኛው ዙርም ከ6ሺህ 2መቶ በላይ ደርዘን ምርቶች እንዲወገዱ ተደርጓል።

ምርቶቹ በገንዘብ ስተመኑ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተወካዩ ጠቁመዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት የንግድና ኢንስፔክሽን ረጉሌሽን ስራ ሂደት ዳይሬክተረት ቡድን መሪ አቶ ዳዊት ይርካዮ ድርጅቱ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፋቸውን ምርቶች በራሱ ለይቶ ለሚመለከተው አካል ያሳወቀ በመሆኑ በንግድ አዋጅና በሸማቾች ጥበቃ መመሪያ መሠረት አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ውስጥ ሳይገባ በትብብር ምርቶቹ እንደሚወገዱ አረጋግጧል።

የንግዱ ማህበረሰብ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ለይቶ ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማሳወቅ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት የጂንካ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ባይስማይ ይህንን የሚያደርጉ የንግድ ድርጅቶችን አመስግነዋል።

የኣሪ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርበው ጠቃቦ በበኩላቸው በዞኑ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፋቸው ምርቶች በሰው ጤና ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ግንዛቤ የመፍጠር እንዲሁም ተላልፈው በተገኙ የንግድ ተቋማት ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ እንዳለ ገልፀዋል።

ነጋደው ማህበረሰብ በድርጅታቸው የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፋቸውን ምርቶች ከመሸጥ እንድቆጠቡና ሸማቹም ማንኛውንም ምርት በሚገዛበትበት ወቅት የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን መለየት እንደምገባ ኃላፊው አሳስበዋል።

ዘጋቢ መልካሙ ቡርዝዳቦ ከጂንካ ጣቢያችን