የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች በዕውቀት የተደራጀ መረጃ ለማኅበረሰቡ በማዳረስ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የዳዉሮ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ ገለጹ

የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች በዕውቀት የተደራጀ መረጃ ለማኅበረሰቡ በማዳረስ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የዳዉሮ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ ገለጹ

“የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በዳውሮ ዞን የሚገኙ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አመራሮችና ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ  ውይይት ተደርጓል ።

በውይይቱ የተገኙ የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ሲሳይ እንደገለጹት የሚዲያ ባለሙያዎችና አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕዝብን ሁለተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በማስተዋወቅና መረጃ በመስጠት በኩል የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

የሥልጠናው ዓላማም የሚዲያ ባለሙያውና አመራሩ አፍራሽ መረጃን ከሚሰጡ የሚዲያ ተቋማት ማኅበረሰቡን በመታደግ በመንግሥት እየተከናወኑ የሚገኙ ልማቶችን በማስተዋወቅ እንዲሁም ሕዝቡን ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማብቃት መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀጣይም በክህሎትና በዕውቀት የተደራጀ የሚዲያ ባለሙያን መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የዞኑ የመንግሥት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ በበኩላቸው የሚዲያ ተቋማት አገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደት አፍራሽ ተልዕኮን ለመመከት እንዲቻል የተጣለባቸው ሕዝባዊና መንግሥታዊ ተልዕኮን በመረዳት ተግባራቸውን ነጻና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ማከናወን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

በሥልጠናው የተገኙ የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ መኩሪያ በበኩላቸው በሥልጠናው አገራዊ፣ ክልላዊና ዞናዊ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የልማት ሥራዎችና የተመዘገቡ ድሎችን በማስተዋወቅ በኩል ለዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

በቀጣይም በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎችና አመራሮች በተቀናጀ ጥረት ለሕዝብ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የልማት ዘርፍ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ሊሠሩ ይገባልም ብለዋል።

በውይይቱ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶች በሰጡን አስተያየት ወቅታዊ አገራዊ፣ ክልላዊና ዞናዊ ኩነቶችን መረዳት የሚያስችል በመሆኑ ለዕለት ተዕለት ተግባራቸው መከናወን ያግዛቸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ እንደሚዲያ ባለሙያና አመራር ማኅበረሰቡ ተጨባጭና ተዓማኒ መረጃን በማግኘት ለጋራ ተጠቃሚነት ተግባሩን እንዲያከናውን የሚያግዝ መረጃን በመስጠት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

ከተለያዩ የዞኑ መምሪያና ወረዳዎች እንዲሁም ከደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትርክ የተገኙ አመራሮችና ሠራተኞች በዞኑ ታርጫ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የሌማት ትሩፋቶችንና በኮርደር ልማት እየተሠሩ የሚገኙ ተግባራትን እንዲሁም በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶች የሚያከናውኑት ሥራዎችን እንዲጎበኙም ተደርጓል።

ዘጋቢ ፡ መሳይ  መሰለ  -ከዋካ   ጣቢያዎች