ከተሞችን ምቹ፣ ውብና ማራኪ በማድረግ የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ፍላጎት መሰረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ከተሞችን ምቹ፣ ውብና ማራኪ በማድረግ የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ፍላጎት መሰረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከተሞችን ምቹ፣ ውብና ማራኪ በማድረግ የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ፍላጎት መሰረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የቤቶችና ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የሙጎ ከተማ በፕላንና በተስተካከለ መንገድ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንድትሆን እየሰራ መሆኑን የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ገልጿል።

በስልጤ ዞን የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ቤቶችና ከተማ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተማም አወል፤ በወረዳው የሚገኙ ታዳጊ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የሙጎ ከተማ በርካታ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ከሚነሱባት ውስጥ አንዷ ከተማ ስትሆን በቅርቡ የከተማዋን ማህበረሰብ ያሳተፈ እና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ሰፊ ውይይት በማድረግ ለረጅም ጊዜ የህዝቡ ጥያቄ ለነበረው ፕላንን መሰረት ያደረገ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ ምላሽ በመስጠት ለከተማዋ እድገት ጉልህ ድርሻ ያለው ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።

በከተማዋ በነዋሪዎቹ ቀና ትብብር የተሰራው የአስር ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ ለከተማዋ እድገት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የነዋሪዎቹን እንቅስቃሴ በማሻሻል ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የሙጎ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ ገራድ ሙጂብ ሱልጣን በበኩላቸው፤ በተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ ህብረተሰቡ እያደረገው ያለው ንቁ ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የሙጎ ከተማን መልካም ገፅታ በመገንባት ለኢንቨስትመንት እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን በማንሳት አሁን ላይ በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫ የተከፈተው የ10 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ ስራ የዚሁ ውጤት ነው ብለዋል።

ለከተማዋ እድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታ አንዱ እንደነበር ያወሱት ስራ አስኪያጁ፤ ህብረተሰቡን ባለቤት በማድረግ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት አሁን ላይ ከ18-20 ሜትር ስፋት ያላቸውንና ፕላንን መሰረት ያደረገ የ10 ኪሎ ሜትር መንገድ ከፈታ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የከተማዋን የገቢ አቅም ማሳደግ፣ የመብራት ዝርጋታ እና ውሃ ማስፋፋት፣ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት፣ ኢንቨስትመንትን መሳብ አና ሌሎች በርካታ እቅዶችን ለማሳካት ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን በማህበር ለተደራጁ መምህራን የቤት መስሪያ ቦታ ተዘጋጅቶ ርክክብ ለማድረግ ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት ኃላፊው፤ በአገልግሎት ዘርፉ ማህበረሰቡን የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት መደረጉን አክለዋል።

አንዳንድ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ንብረታቸውን ያለምንም ካሳ በማንሳት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ማድረግ ያለው ሚና ከፍተኛ እና ቀጣዩን ትውልድ ጭምር ያማከለ በመሆኑ በቀጣይ ለሚደረጉ የትኛውም ተግባራት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ: ሃጀራ ግርማ – ከሆሳዕና ጣቢያችን