ወጣቱ በሚዲያ የሚተላለፉትን መረጃዎች በጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ በመጠቀም እና በማሰራጨት ለሀገረ መንግስት ግንባታው ኃላፊነቱን በተገቢው ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

ወጣቱ በሚዲያ የሚተላለፉትን መረጃዎች በጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ በመጠቀም እና በማሰራጨት ለሀገረ መንግስት ግንባታው ኃላፊነቱን በተገቢው ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወጣቱ በሚዲያ የሚተላለፉትን መረጃዎች በጥንቃቄ እና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ በመጠቀም እና በማሰራጨት ለሀገረ መንግስት ግንባታው ኃላፊነቱን በተገቢው ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ ተናገሩ።

በቤንች ሸኮ ዞን ከሚገኙ ወጣቶች ጋር “ሀገሬን እገነባለሁ፤ ሀላፊነቴን እወጣለሁ” በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቴን በመድረኩ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ ሀገሪቱ አሁን ላስመዘገባቻቸው ለውጦች ዋነኛው የወጣቶች ተሳትፎ ነው።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ ዞኑ በርካታ ሀብቶች ያሉት እንደመሆኑ መጠን ወጣቱ ይህንን የተፈጥሮ ሀብት በተገቢው ተጠቅሞ ወደኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊለውጠው ይገባል።

በተለይም ወጣቱ በግብርናው ዘርፍ፣ በቱሪዝም፣ በትናንሽና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም በማህበራዊ ልማት በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥም ንቁ ተሳታፊ በመሆን የዞኑን የልማት ሂደቶች ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ በበኩላቸው፤ ወጣቶች በሰላማዊ ንግግሮች ላይ በሰላም በመሳተፍ የተዛቡ አመለካከቶችን በማረም መከፋፈልን የሚያበረታቱ ትርክቶችን በመቃወም መግባባትን እና እርቅን በማሳደግ በሰላም አብሮ የመኖርን እና ተባብሮ የማደግን ሁኔታዎች በመፍጠር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል በማለት ተናግረዋል።

ወጣቱ የሚዲያ አጠቃቀሙን በሚዛናዊነት ምክንያታዊ መረጃዎችን በመለየት፣ በመተንተን፣ በመጠቀምና በማሰራጨት ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የወጣቶች ክንፍ ሀላፊ በሆኑት በአቶ ሳኦል ፍቃዱ የውይይት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

በውይይቱ የተሳተፉ ወጣት ተሳታፊዎችም በሀገረ መንግስት ግንባታ እና በሰላሙ ዙሪያ ሀላፊነታቸውን በተገቢው እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ወጣቱ ከተሳሳቱ መረጃዎች እራሱን ሊጠበቅ እንደሚገባ እና ሚዲያን ለበጎ ነገር በማዋል የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

ወጣቱን በገጠር ወደስራ አደራጅቶ ከማስገባት አንጻር ውስንነት መኖርና የብድር አለመመቻቸት ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመው ይህም ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።

የተገነቡ በየቦታው ያሉ የወጣት ማእከላትን አጠናክሮ ወደስራ ከማስገባት አንጻር ጉድለቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በወጣቶቹ ለተነሱት ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን