በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ገለጸ
የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት 2ኛ ዙር 12ኛ አመት 45ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።
የወልቂጤ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈሰሰወርቅ ገብረሰንበት በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት፤ በከተማው የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
ህብረተሰቡ በተለይም በከተማው እየተከናወኑ በሚገኙ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆንም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር ለጉባኤው የባለፉት 9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ በከተማ አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እያከናወኗቸው የሚገኙ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
በከተማው በኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ከብድርና ከሼድ አመላለስ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ከከተማው በወሰደው ብድርና ሼድ ላይ ህጋዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀም ትውልድ እንዲኖር በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።
የገቢ ልማት ዘርፍ መጠናከር ለከተማው ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በመጥቀስ በቀጣይ ዘርፉን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በትኩረት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
ከንግድና ገበያ ልማት አንፃርም በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ አካላት አስፈላጊውን የህግ ስርአት ተከትለው የንግድ እንቅስቃሴአቸውን እንዲያደርጉ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች የሚከናወኑ መሆኑን አቶ ሙራድ አስረድተዋል።
ለጉባኤው በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዘመዴ በቀለ፣ ወይዘሮ ትደነቂያለሽ ወልደሰማያትና ገነት ፍራንሲስ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማ አስተዳደሩ በተለይም በጤና፣ በትምህርትና በቱሪዝም ልማት ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ መልካም ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በኮሪደር ልማትም ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት ለማልማት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው ተግባሩ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ለውጤት እንዲበቃ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
በከተማው ከሰላምና ፀጥታ አንፃር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ በቀጣይም በዘርፉ የተጀመረውን ስራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበለትን የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ስራ አስከያጅ ሹመትን መርምሮ በማጽደቅ ጉባኤውን አጠናቋል።
ዘጋቢ፡ ፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
“አንድነታችንን በማጎልበት የህዝብ ጥቅም የሚያስቀድም ፖለቲካ ማራመድ ይጠበቅብናል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
የሕብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር መሰረት የሆነው ብዝሃነትን በአግባቡ የማስተናገድ ሂደት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑ ተገለፀ
በክረምቱ ወራት ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ አደጋዎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ