የምክር ቤቶችን አቅም በማጎልበት የህዝብ ተጠቃሚነትን ማጎልበት ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ተናገሩ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር ፎረም በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት እና የብሔረሰቦች ምክር ቤት የጋራ ምክክር ፎረም ላይ የተገኙት የክልሉ መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ፤ የምክክር ፎረሙ የክልሉን ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አጋዥ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በእውቀትና በሳይንስ የሚመሩ ምክር ቤቶች ይፈጠሩ ዘንድ የአቅም ማጎልበቻና የምክክር መድረኮች ፋይዳቸው የላቀ ስለመሆኑም ዋና አፈ ጉባኤው አውስተዋል።

ምክር ቤቶች የሰሩትን ስራ በሚገባ ገምግመው ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ያስፈልግ ዘንድ መመካከሩ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ ባውዲ፤ በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የምክር ቤቶችን አቅም ማጎልበት የህዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤው፤ ለዚህ ሀገራዊ ተልዕኮ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አዳማ ትንጳኤ እና የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ እንዲሁም የዞኖችና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ለሁለት ቀናት በሚቆየው የጋራ የምክክር መድረኮች ላይ እየተሳተፉ ይገኛል።

ዘጋቢ: በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን