በምግብ ሰብል ራስን የመቻል አቅም ማሳደግ ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በምግብ ሰብል ራስን የመቻል አቅም ማሳደግ ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን በጉሬጌ ዞን የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ገለፀ።

በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ አብድረሂም ርዳ የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ፓርቲ ፅ/ቤት ሀላፊ እንደገለፁት ብልፅግና ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ በምግብ ሰብል ራስን መቻል መሆኑን ጠቁመው፥ በተለይ የምግብ ሉአላዊነትን የማስከበር ስራ ልዩ ትኩረት ከሚሰጥባቸው መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እንደ ወረዳው መንግስት በርካታ ስራዎች ታቅደው እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት አቶ አብድረሂም ከባለፈው አመት ጀምሮ 2 ሺ 300 ተረጂዎች መለየታቸውን አንስተዋል።

በወረዳው መንግስት ከ10 ሄክታር በላይ ኩታ ገጠም መሬት በማልማት ከ150 ኩንታል በላይ ስንዴ መሰብሰብ መቻሉን ያነሱት ኃላፊው፥ በአርሶ አደር ደረጃ የተለዩ ተረጂዎችን ለመርዳት ከ750 ኩንታል በላይ ሰብል መሰብሰቡን ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት እንደ ቃሪያ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጎመን እና የመሳሰሉት ምርቶች ከሌላ አካባቢ ይመጡ እንደነበረ ያነሱት አቶ አብድረሂም፥ ከግብርና ፅ/ቤት ጋር በጋራ በመሆን ለወጣቶች ግንዛቤ በመፍጠር በተለይም የውሃ አማራጭ ባለባቸው ቦታዎች እንዲመረቱ መደረጉንና ምርቶቹ አካባቢው ላይ በመመረታቸው የገበያው ሁኔታ ማረጋጋት የተቻለበት እንዲሁም ከወረዳው አልፎ ወደ ሌላ ቦታ ማዳረስ መቻሉንም ነው ያነሱት።

የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ የግብርና ፅ/ቤት ምክትል ሀላፊና የእርሻ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መሀመድ ሁሴን በበኩላቸው እንደ ወረዳ በመስኖ 164 ሄ/ር መሬት ማልማት መቻሉን ነው የገለፁት።

ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በመስራት ለአካባቢው ማህበረሰብ እየጠቀሙ መሆኑን ያነሱት አቶ መሀመድ በወረዳው በኩልም የተለያየ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል።

አቶ ሀሚድ ሙሂዲን የኢንጌ ደመካሽ የቤተሰብ ማህበር ሰብሳቢ እንዲሁም አርሶ አደር ጃፈር አለማር በደነብ ቀበሌ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በበጋ ስንዴ ልማት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ናቸው።

ወጣቶቹ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል እየፈጠሩ መሆናቸው አስታውሰዋል።

በወረዳው በኩልም ከመሬት ዝግጅት አንስቶ የግብአት አቅርቦት እንዲሁም ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ወ/ሮ አምርያ ሁሴን እና ሰኢድ አወል በማህበራቱ ውስጥ ሲሰሩ ያገኘናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ፥ ማህበራቶች የስራ እድል እነደፈጠሩላቸውና በዚህም ሙያ ከመማር ባለፈ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰቦቻቸው እየተረፉ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ አስፍር ሙኅዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን