በማዕድን ሀብቶች ላይ ህጋዊ ፈቃድ ወስደው ሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ ዉይይት እየተካሄደ ነዉ

በማዕድን ሀብቶች ላይ ህጋዊ ፈቃድ ወስደው ሥራ ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ ዉይይት እየተካሄደ ነዉ

ማህበራቱ በገቡት ውል መሠረት የአካባቢ ጥበቃና ማህበራዊ ደህንነት ህጎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በትኩረት መሰራት እንዳለበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አሳስቧል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ ወ/ጊዮርጊስ፤ አባቶች በባህላዊ እውቀት ጠብቀው ያቆዩትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠበቅ፣ ማልማትና መንከባከብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአካባቢ ጥበቃና የማህበራዊ ደህንነት ህጎችን ተግባራዊ ማድረግና ከዘርፉ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል አቶ ንጉሴ።

በማዕድን ሥራ የተሰማሩ ማህበራትና ድርድቶች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የአካባቢ ብክለትን በመከላከል በህግና መመሪያው መሠረት መሥራት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ የደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም (ዶ/ር)፤ ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት በተለይም ሰፊ የማዕድን ጸጋ ያለበት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን እምቅ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የማዕድን ሀብት አጠቃቀም መመሪያ በማዘጋጀት ማህበራትን ማሰማራት መቻሉን ገልጸዋል።

በዘርፉ ያሉ ተግባራት በቢሮው ብቻ የሚቻል አለመሆኑን የገለጹት ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም (ዶ/ር)፤ የሚመለከታቸውን አካላት ማሳተፍና በጋራ መሥራት የሚጠይቅ በመሆኑ የጋራ ምክክር መድረክ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በመድረኩ ከክልሉና ሁሉም ዞኖች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት የተገኙ ሲሆን ለውይይት የተዘጋጀው ሰነድ እየቀረበ ይገኛል።

ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን