ከአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ባሻገር ባህርዛፍን ከእርሻ ቦታ በማንሳት በሌሎች ተክል የመቀየሩ ተግባራት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ጎን ለጎን ባህርዛፍን ከእርሻ ቦታ በማንሳት በሌሎች ተክል የመቀየሩ ተግባራት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው አስታወቁ።
በቤንች ሸኮ ዞን በሰሜን ቤንች ወረዳ ባህር ዛፍን ከእርሻ ቦታ በማንሳት በፍራፍሬና በሰብል የመሸፈን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን በጉብኝት ወቅት ለማየት ተችሏል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ከአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ጎን ለጎን በእርሻ ቦታ ላይ ያለውን ባህር ዛፍ በማንሳት በፍራፍሬና በሰብል የመተካት ስራ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጎበኙበት ወቅት እንደገለፁት ተግባሩ የአርሶ አደሩን ገቢ ምንጭ ከማሳደግም በላይ በክልሉ ተረጂነትን ለማስወገድና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን በሰሜን ቤንች ወረዳ ባሉት ቀበሌዎች እየተሰራ ያለው ባህር ዛፍን በፍራፍሬ የመተካት ስራ ለክልሉ አካባቢዎች ምርጥ ተሞክሮ ከመሆንም ባለፈ በበጋ ወቅት የተከናወኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎችን በስነ ህይወታዊ ስራ ከማስደገፍ አንጻር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አቶ ማሰረሻ ተናግረዋል።
በተለይም በክልሉ የመሬት መጠቀሚያ ግብር አዋጅ ላይ ባህር ዛፍን በእርሻ መሬት መትከል ለየት ያለ የመሬት መጠቀሚያ ግብር እንዲከፈል ሲደረግ ባህር ዛፍ በእርሻ መሬት ላይ በስፋት የሚካሄደውን ተከላን ለመግታት የሚያግዝና በቀጣይም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉበላ በበኩላቸው ከአርሶ አደሩ ጋር በመግባባት በወረዳው በ21 ቀበሌዎች ከ3ሺህ ሄ/ር በላይ መሬት ባህር ዛፍን በማስነሳት በሙዝና በበቆሎ ሰብል መሸፈኑን ገልጸው የሰሪቲ ቀበሌ 1ሺህ ሄ/ር ማሳ ለዚሁ ማሳያ እንደሆነም ተናገረዋል።
የተሰሩ ስራዎችን ቀጣይነት ባለው መንገድ በመደገፍ፣ በማበረታታት እና ከገበያ ጋር አስተሳስሮ መስራት ከአመራሩ፣ ከባለሙያውም ሆነ ከባለድርሻ አካላት የሚፈለግ ተግባር እንደሆነም ኃላፊው አሰረድተዋል።
በመጨረሻም በወረዳው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም(FSRP) የተገነባው የቢር የፍራፍሬ አትክልት የግብይት ማዕከላትና የቦሶቃ የችግኝ ጣቢያ ጉብኝትም ተደረጓል።
ዘጋቢ: አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሪጅን በሚዛን ዲስትሪክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው 9ኛው የምስለ ችሎት ውድድር በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ