በክልሉ እየተካሄደ ያለው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻልም ባለፈ የገበያ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለፀ

በክልሉ እየተካሄደ ያለው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻልም ባለፈ የገበያ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለፀ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የአብይ ኮሚቴ የ2017 ዓ.ም የ9 ወራት አፈፃፀም እና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ ላይ በሚዛን አማን ከተማ መክረዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ፕሮግራሙ በሁሉም ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል ባለፈ የገበያ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናገረዋል።

ፕሮግራሙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅና የማስረጽ፣ ለአርሶ አደሮች ግብዓት በማቅረብ፣ በሁሉም ዘርፍ የኤክስቴንሽን ድጋፍ ማድረግ፣ የመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋታና አጠቃቀም በማሻሻል ፣ የግብይት ማዕከላትን በመገንባት፣ ገበያ ትስስር በማሻሻል እንዲሁም የአቅም ግንባታና ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ አበረታች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አቶ ማስረሻ ተናግረዋል።

በ9 ወራት 587 ሄ/ር መሬት በአነስተኛ መስኖ ለምቶ 1332 አባወራን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል

በገበያ ትስስር 47,558 እንስሳትን መገበያየት የሚያስችል 3 የእንስሳት ገበያ ማዕከል መገንባቱን ተመላክቷል ።

ፕሮግራሙ በክልሉ በስድስቱ ዞኖችና 15 ወረዳዎች 368 ቀበሌዎች የሚተገብርና ሰፊ ህብረተሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ለበለጠ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን በክልል ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ሁሰን ተናገረዋል።

በውይይቱ ላይ በፕሮግራሙ አበረታች ውጤት እየተመዘገቡ መሆኑን በማንሳት የግብርና ባለሙያዎች አቅም ግንባታ፣ በእንስሳት ሀብት ጤና አያያዝና ጥራት፣ በመሬት አሲዳማነት፣ በማርና ቡና ምርትን መጨመርና ጥራት እንዲሁም ግብይት፣ የግንባታ ዲዛይንና በጊዜና በጥራት ጀምሮ ከማጠናቀቅ አኳያ በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት አንስተዋል።

በተለይም ሴቶች በተለያዩ ዘረፍ ተሰማርተው የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረው የበለጠ እንዲጎልበት ቅንጅታዊ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት መኩሪያ በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል።

የክልሉ አብይ ኮሚቴ በምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የ2017 ዓ.ም የ9 ወራት አፈፃፀም እና የ2018 ዓ.ም ጠቋሚ ዕቅድ ላይ ለተነሱ ጉዳዮች ከመድረኩና ከሚመለከታቸዉ አካላት ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ተጠናቋል።

ዘጋቢ ፡ አብዲሳ ዮናስ-ከሚዛን ጣቢያችን