በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቀቤና ልዩ ወረዳ በተያዘው የበልግ ምርት ወቅት ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የልዩ ወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

በምርት ዘመኑ በበልግ እርሻ የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን የልዩ ወረዳው አርሶ አደሮች ገልጸዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብድልሽኩር ደሊል፤ ልዩ ወረዳው የበልግ እርሻ በስፋት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚለማና ከዚህም 9 ሺህ ሄክታር መሬት ያህሉ በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት ሀላፊው አሁን ላይ 23 ሺህ 350 ኩንታል ማዳበሪያ ቀርቦ ዘር መዝራት መጀመሩን ጠቁመዋል።

በልዩ ወረዳው የግብርና ሜካናይዜሽን ፍላጎት እያደገ መምጣቱንና 32 ትራክተሮችን በመጠቀም በ13 ቀበሌዎች በኩታገጠም ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ በማመላከት በዚህም አፈጻጸሙ አበረታች መሆኑን ነው ያስረዱት።

የበልግ እርሻ በተለይም በሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንፃር ትልቅ ሚና እንዳለው ያነሱት አቶ አብድልሽኩር፤ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የልዩ ወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኸይሩ ነስሩ፤ ለአርሶ አደሩ የክህሎት ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ የቅርብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የወረዳው አርሶ አደር ከባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር በመተግበር የግብዓት እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን የገለፁት ሃላፊው፤ በዚህም ተጠቃሚነቱ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

አቶ መሐመድ አሚን ሸምሱና አብድልሰመድ ሀዲ የፈረጀቴና ሩሙጋ ቀበሌያት የግብርና ባለመያዎች ሲሆኑ አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ከባለሙያ የሚያገኘው የክህሎት ስልጠና ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን ተከትሎ ተጠቃሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይገኛል ነው ያሉት።

በተለይም አሁን ላይ የየቀበሌው አርሶ አደሮች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በበልግ እርሻ ላይ በተለያዩ አደረጃጀቶች በመታገዝ በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በልዩ ወረዳው ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ሙባሪክ ሀዲ፣ መሐመድኑር አህመዲን፣ ሸምሱ ከድር እና አብደላ ሳኒ የፈረጀቴና ሪሙጋ ቀበሌ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡

በሰጡት አስተያየት በምርት ዘመኑ በበልግ እርሻ ወቅት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መግባታቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም ከምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት አንጻር በዘንድሮው የምርት ዘመን የተሻለ አቅርቦት ስለመኖሩም አንስተዋል።

በኩታ ገጠም በመስራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥና ገበያን ለማረጋጋት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውንና ለዚህም ውጤታማነቴ በኩታገጠም ጠንክረው እየሰሩ አንደሚገኙ አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን