የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በኦዲት ወቅት በሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቡታጅራ ከተማ ውይይት ማካሄድ ጀመረ

‎የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ፈዲላ አደም፤ የመስሪያ ቤቱ መቋቋም ዋና ዓላማ የሕዝብና የመንግስት ሀብትና ንብረት በትክክል ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው ብለዋል።

‎ለዚህም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መድረክ ፈጥሮ መወያየት ያለው ሚና የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።

‎የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በአዋጅ 27/2016 በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረት እንዲሁም የተመርማሪዎች ግዴታ፣ የኦዲት አይነትና በኦዲት ወቅት በሚያጋጥሙ ችግሮች ዙሪያ በክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የኦዲት ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክተር በአቶ አበራ ጫኬቦ መወያያ ሰነድ ለውይይት ቀርቧል።

‎ካሉት 5 የኦዲት አይነቶች በክልሉ ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ የተመላከተ ሲሆን የመረጃ ስርዓት ወይም IT ኦዲት ብቻ ተግባራዊ መደረግ አለመጀመሩ ተገልጿል።

‎በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ መነቴ ሙንዲኖ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ፣ የክልሉ ዋና ኦዲተር ወ/ሮ ፈዲላ አደም፣ የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አመራሮች፣ የሁሉም ዞንና ልዩ ወረዳዎች ዋና አፈ ጉባዔዎች፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አብደላ በድሩ