በመስኖ ተቋማት ጥናትና ዲዛይን እና በግንባታ ተቋማት አስተዳደር ዘርፍ የተሻለ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በበጀት አመቱ በመስኖ ተቋማት ጥናትና ዲዛይን እንዲሁም በግንባታና በተቋማት አስተዳደር ዘርፍ የተሻለ ስራ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

በክልሉ ከ393 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች ለምርቃት መብቃታቸውን ተመላክቷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ እንዳሉት በተያዘው በጀት አመት በመስኖ ተቋማት ጥናትና ዲዛይን እንዲሁም በግንባታና ተቋማት አስተዳደር የተሻለ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ በሶላር ፓምፕ ከሚለሙ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ግድብ ጥናት ያሉ ስራዎች ላይ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፥ ከዚህ ቀደም የመስኖ መረጃዎች የተሳሳቱ በመሆናቸው መረጃውን በማጥራት በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደገፈ ቆጠራ በማካሄድ ትክክለኛ መረጃ ማደራጀት መቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በብላቴ ወንዝ ላይ የመስኖ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው በበጋ ወቅት የውሃ እጥረት እንዳይገጥማቸው በውሃ አጠቃቀም ላይ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባቢያ ሰነድ የመፈራረም ስርኣት በመካሄዱ ከዚህ ቀደም ይገጥም የነበረው የውሃ አጠቃቀም ችግር መቀረፉን አስረድተዋል።

በበጀት አመቱ 16 የመስኖ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙና ሰፋፊ ወንዞች በሌሉባቸው መዋቅሮች 70 ሶላር ፓምፖችን በመትከል በተገኘው የውሃ አማራጭ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በበጀት አመቱ ዘጠኝ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እስካሁን ባለው ሂደት 10 የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አምስቱ ተመርቀዋል።

በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ቱባና ተሊሎ ቀበሌ የተመረቀው የሬቡ የመስኖ ፕሮጀክትም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመጠናቀቁ ልምድ የሚወሰድበትና ፕሮጀክቶች ክትትል ከተደረገላቸው በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ እንደሚችሉ ያሳየ ነው ብለዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ 70 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችልና 280 አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና በ70 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የተገነባ መሆኑን አስታውሰዋል።

የሬቡ የመስኖ ፕሮጀክትን ጨምሮ ወልዲያ፣ ኮሾ ኤልኩሜና አመካ የመስኖ ፕሮጀክቶች የተመረቁ ሲሆን 765 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸውና 3ሺ 60 አባወራዎችን የሚያስጠቅሙ ናቸው ብለዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ 393 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉን ስራአስኪያጁ ጨምረው ገልጸዋል።

የመስኖ ተቋማት ከተገነቡ በኋላ የማስተዳደርና ጥቅም ላይ የማዋል ችግሮች ይስተዋላሉ ያሉት ኢንጂነር ካሳዬ ችግሩን ለመቅረፍም የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ስልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ መላኩ ንማኒ – ከወልቂጤ ጣቢያችን