ጂንካ ዩንቨርሲቲ የመጀመሪያውን አለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ አካሄደ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ዩንቨርሲቲ የመጀመርያውን አለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ “ለአለም አቀፍ የቱሪዝምና የግብርና ተግዳሮቶች ሀገራዊ መፍትዎች” በሚል መሪ ሃሳብ በጂንካ ከተማ አካሄደ።

በጂንካ ዩንቨርስቲ የምርምር ስነ-ምግባር ስርፀት ዳይሬክተር ዶክተር አንዳርጌ ዘውዴ እንደገለፁት ዩንቨርሲቲው ከተቋቋመበት አመት ጀምሮ ከ240 በላይ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቁመው፥ በምርምር ኮንፍረንሱ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት በ14 የምርምር ሥራዎች ላይ መወያየታቸውን አስረድተዋል።

በጂንካ ዩንቨርስቲ የአካዳምክ ምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር የማህበረሰብ አገልግሎት የም/ፕሬዝዳንቱ ተወካይ መምህር ኢብራሂም ጀማል በበኩላቸው፥ ዩንቨርስቲው ከተቋማት ጋር በመቀናጀት የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን እና ቱሪዝምን ቀጣይነት ላለው ዕድገት ለማዋል የሚያግዙ ለአለም አቀፍ ተግዳሮቶች ሀገራዊ መፍትሔዎች ላይ በማተኮር የምርምር ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገር በቀል ዕውቀት ላይ በማተኮር በቱሪዝምና በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረጉ የምርምር ሥራዎችን ዩንቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኢብራሂም ጀማል አክለዋል።

ጥናታዊ ፅሁፉን ካቀረቡ ተመራማሪዎች መካከል የወልቂጤ ዩንቨርስቲ መምህር ፀጋማሪያም ዱላ እና የአርባምንጭ ዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር ይስሐቅ ኬቺሮ በጋራ እንደገለፁት የግብርናን ሆነ የቱሪዝምን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን ማቅረባቸውን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን