ሀዋሳ፡ ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህዝብን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሊሰራ እንደሚገባ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡
የስልጤ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 29ኛ መደበኛ ጉባዬውን አካሄዷል።
የዞኑ ዋና አፈ ጉበኤ ወ/ሮ መህዲያ ቡሴር ባስተላለፉት መልዕክት ምክር ቤቶች የህዝብ ሉዓላዊነት የሚከበርባቸው ከመሆንም ባሻገር የህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሚሰራበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የበጀት አመቱን የዘጠኝ ወር ሪፖርት ለምክር ቤት አባላት ያቀረቡት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መቻሉን አመልክተው፥ ይህም ከመደበኛው የእርሻ ወቅት በተጨማሪ የበጋ መስኖ እና በፀደይ ወቅት እርሻ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ አዝርዕትና ፍራፍሬ በማልማት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።
በ2016/17 የምርት ዘመን በበልግና በመኸር እርሻ 119ሺ 858 ነጥብ 8 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ የሰብል አይነቶች በማልማት 8 ሚሊየን 957ሺ 630 ነጥብ 8 ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ገልፀዋል።
በቡናና ቅመማ ቅመም ኢንሼቲቭ በተከናወኑ ስራዎች በተለይም ለሮዝማሪ ቅመማ ቅመም በተሰጠው ልዩ ትኩረት ወደ ውጭ በመለክ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት፣ በማአጤመ ተጠቃሚ አባላት ከማሳደግ ባለፈ የአቅም ውስንነት ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት ክፍያ በመፈፀም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፥ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግ በተጨማሪ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል።
የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የተጠናከራ ስራ መሰራቱንም በመጠቆም።
በትምህርቱ ዘርፍም ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው ዞኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ በግብርና፣ በእንቨስትመንት፣ በአገልግሎት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉ ተመላክቷል።
ማህበረሰቡ ያለውን ጠንካራ የስራ ባህል አጠናክሮ በማስቀጠልና የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር የተለየዩ የልማት ስራዎችን ከግብ ለማድረስ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
የምክርቤቱ አባላትም ከቀረበው ሪፖርት መነሻ አስተያየት እና ጥያቄዎችን አንስተው በባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ: አሚና ጀማል እና ሙጂብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የብልጽግና መንግስት ባለፉት አመታት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በማስጀመር ጠንካራ የሆነ ስራ እየሰራ ነው – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዱራሜ ክላስተር የግብርና ሴክተር ባለሙያዎች “የመሐሉ ዘመን” በሚል ርዕስ ወቅታዊና ሀገራዊ ሰነድ ላይ ውይይት አካሄዱ
ከተማ አስተዳደሩ በተለያየ ስፖርት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ገለጸ