የዲላ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ታሪፍ አሻሻለ
በጌዴኦ ዞን የዲላ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻልን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አጸደቀ
ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 15ኛ አስችኳይ ጉባኤ በጌዴኦ ዞን በዲላ ከተማ አካሂዷል።
ምክር ቤቱ እያደገ የመጣውን የህብረተሰቡን የመልማት ፍላጎትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማያረጋግጥ ከሚያግዙ በርካታ ሥራዎች መካከል የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ታሪፍ ማሻሻልና የደንብ አስከባሪ አደረጃጀቶችን ለአብነት አመላክቷል።
የዲላ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በኪዩቢክ ሜትር ሲያሰከፍል የነበረውን ታሪፍ ለማሻሻል የዕቃ ዋጋ መናር፣ የነዳጅና የኤሌትሪክ ክፍያ መጨመር እንዲሁም ሌሎች በርካታ ምክንያት እንደሚጠቀሱ የከተማው አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃ ኡዶ ተናግረዋል።
በከተማው የተገነባው ትልቁ የውሃ ፕሮጀክት በብድር የተገነባና ቀሪ ሥራዎች የሚጠብቁት ነው ያሉት አቶ ፍስሃ፣ ብድሩን ለመመለስና ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከዚህ በፊት በሜትር ኪዩቢክ ለውሃ አገልግሎት ይከፈል ከነበረው 15 ብር ወደ 41 ብር ታርፍ ማሻሻያ መደረጉን ተናግረዋል።
የዲላ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ያረጁ መስመሮችና የውሃ ቆጣሪዎችን በማሻሻል ውሃ ላይ እየደረሰ ያለውን ብክነት ለመቀነስ እየሠራ ነው ብለዋል።
የዲላ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ከበደ በበኩላቸው፥ በከተማው ካለው ህዝብ ብዛት መነሻ ያለው ፖሊስ ኃይል በቂ ባለመሆኑ የከተማን ሰላምና ደህነት ለመጠበቅ የደንብ አስከባሪ ማደራጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።
ይህም በከተማው በየጊዜ እየተስፋፋ ያለው ህገ ወጥ አሰራሮችንና ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ለፖሊስ አጋዥ ኃይል በመሆን ተደራሽነት ያሰፋል ያሉት ኃላፊው በቀጣይ መተዳደሪያ ደንብ እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል።
ዲላ ከተማ ላይ አሁን ያለውን ሰላም ለማጽናት የደንብ አስከባርን ማደራጀት ፋይዳ የጎላ መሆኑን የገለጹት አቶ አዲሱ ህብረተሰቡ ለሰላም ዘብ በመቆም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የደንብ አስከባሪ አደረጃጀት ላይ ምልመላ ሲደረግ በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባ ምክር ቤቱ አሳሰበዋል።
የምክር ቤት አባላት የህዝብ ተወካይ እንደመሆናቸው መጠን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጣለባቸውን አደራ በትጋት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የዲላ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፈትለወርቅ በቀለ አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ታርፍ ማሻሻል፣ የደንብ አስከባሪ አደረጃጀት መመሪያ እና በከተማው ውሰጥ ለሚገኙ ሰባት አደባባይ የተሰጡ ስያሜዎች ላይ በስፋት ተወያይተው በማጸድቅ ጉባኤውን አጠናቋል ።
ዘጋቢ: ተስፋዬ ጎበና – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በሚዛን አማን ከተማ አረንጓዴ አሻራ አሳረፉ
የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ነው
በክልሉ በተያዘው የበልግ ወቅት በኩታገጠም ሩዝና በቆሎ እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች ተስፋ ሰጪ የሆነ የምርት ውጤት እንድናይ አስችሎናል አሉ።