የስልጤ ዞን ምክር ቤት ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለምክር ቤት አባላት የአቅም ግንባታ ስልጠና በወራቤ ከተማ እየሰጠ ይገኛል
የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ መህዲያ ቡሴር እንደገለፁት፤ ለምክር ቤት አባላት በየ ጊዜው የሚሰጠው ስልጠና የስራ ተነሳሽነትን በማሳደግ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን ያግዛል።
የምክር ቤት አባላት ህብረተሰቡ የሚያነሷቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ ሚና አላቸው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ፤ ስልጠናው በህገ መንግስትና በፌደራሊዝም ምንነትና ተግባር ላይ በቂ እውቀት እንዲኖር ለማድረግ አጋዥ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ስልጠናው የምክር ቤት አመሰራረት እና በፌደራሊዝም ምንነት ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን የምክር ቤት አባላት መብትና ግዴታ፣ ስነ ምግባርና ተግባር በተመለከተ የተዘጋጀ ሰነድ በዞን ፍትህ መምሪያ አቃቢ ህግ አቶ ነጃ ሰልማን ቀርቧል።
ከዚህ በተጨማሪ የምክር ቤቶች ተግባርና ኃላፊነት ላይም ዝርዝር ጉዳዮች በስልጠናው ተነስተዋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አባስ ሉቅማን በበኩላቸው፤ የምክር ቤት አባላት መብትና ግዴታቸውን በማወቅ ህብረተሰቡ የጣለባቸውን ኃላፊነት በተገቢው መወጣት እንዲቻል ስልጠናው ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የጋራ ሀገራዊ ትርክት ለመገንባት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ያሉት የፖለቲካል ሰይንስ መምህሩ፤ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህላችንን በማሳደግ ረገድ የምክር ቤት አባላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በስልጠና መድረኩ ላይ የተገኙት የምክር ቤት አባላት በዕለቱ የቀረበውን ሰነድ መነሻ በማድረግ ከህገ መንግስትና ፌደራሊዝም ምንነትና አተገባበር ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ስልጠናው የአባላቱን አቅም በማጎልበት የማስፈፀም አቅም ይጨምራል ብለዋል።
በስልጠና መድረኩም የዞኑ ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ መህዲያ ቡሴር፣ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ነዒማ ሙኒርና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ነስሮ አለሙን ጨምሮ የወራቤ ዩኒቨርሲቲ አሰልጣኝ መምህራንና የዞኑ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።
ዘጋቢ: ሙጂብ ጁሃርና አሚና ጀማል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሪጅን በሚዛን ዲስትሪክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው 9ኛው የምስለ ችሎት ውድድር በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ