ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው

ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት “ኢኮኖሚያዊ ዕውቀታችንን በመጠቀም ለድህነት ቅነሳ መስራትና ማህበራዊ ህይወታችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ” በሚል መርህ ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚህ ለ6ኛ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው ኮንፈረንስ ላይ 30 የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል።

በኮንፈረንሱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ የኮንፈረንሱ ዓላማ በጥናታዊ ስራዎችና ግኝቶቻቸው ላይ ልምድና ተሞክሮ መለዋወጥ ነው።

የሚቀርቡ የጥናትና የምርምር ውጤቶች ሀገሪቱ እያስመዘገበች ለምትገኘው ፈጣን እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም አመላክተዋል።

ሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ዕውቀትን በመጠቀም በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማስመዝገብ እንዲቻልም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዮሀንስ ገብሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ውጤታማነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

ለዚህ ውጤታማነት ደግሞ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ትልቅ ሚና እንደተጫወተ አንስተዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ 30 የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ጠቁመዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለ2 ቀናት በሚካሄደው ኮንፈረንስ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር አክመል መሐመድ (ዶ/ር)፤ ከሀገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ጥናት አቅራቢዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መምህራን እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን