በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሞሪንጋ ጂን ባንክ ለማቋቋም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሞሪንጋ ጂን ባንክ ለማቋቋም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን ደንባ ጎፋ ወረዳ የሞሪንጋ ጂን ባንክ በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ለማቋቋም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

ከነገ ትውልድ የተበደርነውን የብዝሃ ህይወት ሀብታችንን በአግባቡ ይዘን ለተበደርነው ትውልድ ለማስረከብ በሚያስችል ጉዳዮች ዙሪያ በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናም ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲቱት የሀዋሳ ብዝሀ ህይወት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አገጠ ጀረኔ የብዝሀ ህይወት ቀን በየዓመቱ ግንቦት 22 ቀን የሚከበረውን ምክንያት በማድረግ የብዝሀ ህይወት ምንነት፣ የብዝሀ ህይወት ሀብት አጠባበቅና ብዝሀ ህይወትን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ያለውን መጤ ወራሪ አረሞች ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር የታለመ ነው ብለዋል።

ብዝሃ ህይወት ማንኛውም በዚህ ፕላኔት ህይወት ያሉ ነገሮችን የሚያጠቃልል መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ብዝሃ ህይወት ለሰው ልጅ መድኃኒት፣ ምግብ፣ ውሃ፣ መዝናኛ እና ሌሎች በርካታ ጥቅሞች መኖሩን አብራርተዋል።

ብዝሃ ህይወትን የሚያጠፉ ነገሮች መነሻቸው የሰው ልጅ በመሆኑ ደንን በመጨፍጨፍ፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ሲሰራና ከተማን ለማስፋፋት ሲፈለግ ብዝሃ ህይወትን ግንዛቤ አለማድረግ ችግሮች መኖሩን ጠቁመው የመሬት መንሸራተትና ለተለያዩ ተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋልጥ መሆኑን አስረድተዋል።

ማዕከሉ በደምባ ጎፋ ወረዳ ሀለኮ ወይም የሞሪንጋ ጂን ባንክ በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ስራው የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲቱት የሀዋሳ ብዝሃ ህይወት ማዕከል የደን ተመራማሪ አቶ ግዛው በጅጎ ፓርቲንየም የተሰኘ መጤ ወራሪ አረም በ1970ዎቹ አከባቢ በምስራቅ አከባቢ ወደ ሀገራችን መግባቱን ጠቁመው አሁን ከወላይታ ጀምሮ በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳን የወረረ አደገኛ አረም መሆኑን አስረድተዋል።

እምቦጭ፣ ፕሮሶፊስ፣ የወፍ ቆሎ እና ፓርቲንየም የተሰኙ አደገኛ አረሞች በደቡብ ክልል በብዛት የሚገኙ ናቸው ያሉት ተመራማሪው፥ ፓርቲንየም አረም ብዙ ዘር በማምረት በጥቂት ጊዜ ውስጥ በንፋስና በተለያዩ መንገዶች በርካታ ቦታ የመሰራጨት፣ ድርቅን የመቋቋም አቅም መኖር፣ ከውስጣቸው የሚያመነጩት ኬሚካል በአጠገባቸው ያለውን ብዝሃ ህይወትን መግደልና ብቻውን የመኖር አቅም አላቸው ብለዋል።

የግንዛቤ ስራው በቀድሞ ደቡብ ክልል በአሁኑ አራት ክልሎችን እና ከኦሮሚያ ክልል ቦረናና ጉጂ ዞኖች ያቀፈ መሆኑን ጠቁመው በቦረና ዞን፣ በጎፋ ዞን በደምባ ጎፋ ወረዳ በርካታ ቦታዎች እንዲሁም ሎካ ዓባያ ላይ እምቦጭ የማስወገድ ስራዎች መሰራቱን አስረድተዋል።

የደምባ ጎፋ ወረዳ ምክትል አስተዳደርና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ አላ ለአየር ንብረት የማይበገር አከባቢን ለመፍጠር በአረንጓዴ አሻራ ሥራዎችን በማጠናከርና የአፈር መሸርሸርን በትኩረት መከላከል እንደሚገባ ገልፀው ማዕከሉ በብዝኃ ህይወትና መጤ ወራሪ አረሞች ላይ የሰጠውን ግንዛቤ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም አሳስበዋል ።

የወረዳው ደን አካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመሰገነ አባይነህ የሀዋሳ ብዝሃ ህይወት ማዕከል በወረዳው 81 ሄክታር መሬት በመረከብ ዶጫ ዳንባላ ቀበሌ በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ሞሪንጋ ዘር የማባዛት ስራ መጀመሩን አንስተው በሚያዝያ ወር ከ20 ሺህ በላይ የሞሪንጋ ችግኝ መተከሉን አስረድተዋል።

ተሳታፊዎች በማዕከሉ በኩል ከተሰጠው ስልጠና በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረው በቀጣይ ወደ ማህበረሰቡ በመውረድ በትኩረት ለመስራት ቃልም ገብተዋል።

ዘጋቢ: ኢያሱ አዲሱ – ከሳውላ ጣቢያችን