መደበኛና በዘመቻ የሚሰጡ የክትባት አገልግሎቶች የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ መላው ህዝብ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
ሀዋሳ፡ ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያየ ጊዜ ለህፃናት በመደበኛና በዘመቻ መልክ የሚሰጡ የክትባት አገልግሎቶች የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ መላው ህዝብ የድርሻውን እንዲወጣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
ከፊታችን ግንቦት 06/2017 ዓ/ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻን በማስመልከት ለሚዲያ አካላት በጂንካ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
የህዝቡ ጤና ተጠብቆ በሰፊው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ እናቶችና ህፃናት ሥርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት እና የክትባትና ህፃናት ጤና ክፍል አስተባባሪ አቶ አብዱልቃድር ሁሴን ገልፀዋል።
ከፊታችን ግንቦት 6/2017 ዓ/ም ጀምሮ የሚሰጠው የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት የህፃናት ህመምና ሞት የሚያስከትለውን ለማስቀረት ታስቦ ነው ብለዋል።
ዕድሜያቸው ከዘጠኝ ወራት እስከ 59 ወራት ለሆኑ ህፃናት ክትባቱ እንደሚሰጥ የገለፁት ሀላፊው ከዚህ በፊት የተከቡም ይሁን ያልተከተቡ ህፃናት በክትባት ዘመቻው ተደራሽ ይሆናሉ ሲሉም ተናግረዋል ።
ዘመቻው ከመደበኛ የህክምና አገልግሎት መስጫ ጤና ተቋማት በተጨማሪ ጊዜያዊ የክትባት ጣቢያዎች ተከፍተው የክትባት ዘመቻው እንዲሰጥ እንደሚደረግም ተገልጿል ።
በዚህም ከ1 ሚሊዮን 237 ሺህ 563 ህፃናት የክትባት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ታስቦ ዘመቻው እንደሚሰጥ ኃላፊው ተናግረዋል ።
በዘመቻው መደበኛ ክትባት ያልተከተቡ እና ያቋረጡ ህፃናት መለየና መከተብ፣ የታመሙ ህፃናት ልየታና ወደ ጤና ተቋም መላክ፣ አጣዳፊ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ልየታና ወደ ጤና ተቋም መላክ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ መስጠት፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትል ህክምና ክኒንና መሰል አገልገሎቶች እንደሚሰጡ የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ ናቸው።
መላው ህብረተሰብ እና ሚዲያ አካላት ዘመቻው የተሳካ እንዲሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ ናፍቆት ጥሪ አቅርበዋል።
በግንዛቤ ስልጠናው የተሳተፉ የሚዲያ አካላትም ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ ወቅታዊ የሆነውን የተቀናጀ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን እንደሚሠሩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ኩፍኝ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በበሽታው ከተያዘ ሰው አፍንጫና ጉሮሮ በሚመጣ ፈሳሾች ንኪኪና በትንፋሽ አማካኝነት እንደሆነ ተገልጿል ።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ፈጣንና ቀልጣፋ መረጃን ተጀራሽ በማድረግ የመንግስትና የማህበረሰቡን ተግባቦት ይበልጥ ለማጠናከር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና የጎላ መሆኑ ተጠቆመ
ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው
በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሞሪንጋ ጂን ባንክ ለማቋቋም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ