ከ19ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ወደ ተግባር መግባታቸውን ተገለጸ

ከ19ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ወደ ተግባር መግባታቸውን ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 29/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጎፋ ዞን በ2017 የበጀት ዓመት ከ19ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ወደ ተግባር መግባታቸውን የዞኑ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ አስታወቀ

በዞኑ ደንባ ጎፋ ወረዳ በሰብል ልማትና በሌማት ትሩፋት የተሰማሩ ወጣቶች የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ ተደርጓል፡፡

በደንባ ጎፋ ወረዳ ቦርዳ፣ ዶንቤ፣ ካርዛ እና አዋንዴ ዶርማሌ ቀበሌያት በአንድ ቀን ጫጬት፣ በእንቁላል ጣይ ዶሮ በበቆሎና በሰሊጥ ምርት የተሰማሩ ወጣቶች ከስራ ጠባቂነት ወደ ስራ ፈጣሪነት በመሸጋገራቸ ኑሯቸውን ለማሻሻል የተሻለ ተስፋ አንዳላቸው ተናግረዋል።

የደንባ ጎፋ ወረዳ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ብርሃኑ፤ በወረዳው 3ሺህ 600 ወጣቶችን በተለያዩ የስራ መስኮች ለማሰማራት ታቅዶ 3ሺህ 200 ወጣቶችን በቋሚና 650 ወጣቶችን በጊዜያዊ የስራ ዘርፎች ማሰማራት ተችሏል ብለዋል።

500 ወጣቶች በ100 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው በሰብል ልማት የተሰማሩ ሲሆን 20 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በሰሊጥ የተሸፈነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ አራታ በበኩላቸው፤ ለወጣቶቹ ከ90 ሄክታር መሬት በላይ መተላለፉንና ከ200ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ በሰብል ልማት ለተሰማሩ ወጣቶች ማሳቸው በትራክተር እንዲታረስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞገስ መኩሪያ በበኩላቸው፤ በዞኑ በ2017 የበጀት ዓመት 31ሺህ ስራ አጥ ወጣቶች የተለዩ ሲሆን ከ19ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ለወጣቶቹ 355 ሄክታር ለመስሪያ የሚሆን መሬት መሰጠቱን አንስተው ወጣቶቹ በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል በትጋት እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሰብል ልማትና በሌማት ትሩፋት የተሰማሩ ወጣቶች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን