ወቅቱ ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ የሚከሰትበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቆመ
በዳውሮ ዞን የከጪ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የወባ በሽታ መስፋፋትን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በአካባቢያቸው የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ በተካሔዱ ተግባራት ስርጭቱን ለመቀነስ ተችሎ የነበረ ቢሆንም መልሶ የማገርሽት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ጤና አጠባበቅ ጣቢያ አግኝተን ካነጋገርናቸው ታካሚዎች መካከል አስር አለቃ ተስፋዬ አግዜ፣ አንዳርጌ ሀብቴ እና ወ/ሮ አየለች ተናግረዋል፡፡
እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ በአሁኑ ሰዓት በበሽታው የመያዙ ሁኔታዎች እየሰፋ ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የመድኃኒት እጥረቶች ተቀርፎ ለበሽታ መከላከል ስራዎቹ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የከጪ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ኮቾ በበኩላቸው፤ ወቅቱ ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ የሚከሰትበት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አክለውም የበሽታውን መስፋፋትና ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በርካታ ሰራዎችን በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በባለፉት ወራቶች የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ስራ ላይ ጥሩ ለውጦች ቢታዩም ከየካቲት ወር ወዲህ ባሉት ወራቶች ውስጥ የመስፋፋቱ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን በከጪ ወረዳ የጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ዘርሁን ገልጸዋል።
በወረዳው ሁለት ጤና ጣቢያዎች ብቻ መኖሩ እና የባለሙያ እጥረት መኖሩ እንዲሁም የመድኃኒት ስርጭት በወቅቱ ለማድረግ የአቅርቦት ችግሮች ይበልጥ የወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ስራ እንዳይሰራ ማነቆዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በቀጣይ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የበሽታውን መስፋፋትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ዘጋቢ፡ አፈወርቅ ኦሹ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በሚዛን አማን ከተማ አረንጓዴ አሻራ አሳረፉ
የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ነው
በክልሉ በተያዘው የበልግ ወቅት በኩታገጠም ሩዝና በቆሎ እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች ተስፋ ሰጪ የሆነ የምርት ውጤት እንድናይ አስችሎናል አሉ።