በዘመናዊ የከብት እርባታ ስራ ዘርፍ የተሰማራችው ባለሀብት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን እያሳደገች መምጣቷን ገለፀች
በቤንች ሸኮ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ ኩጃ ከተማ በዘመናዊ የከብት እርባታ ስራ ዘርፍ የተሰማራችው ባለሀብት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን እያሳደገች መምጣቷን ገለፀች።
በወረዳው ያለው የእንስሳት እርባታ ስራ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተጠናከረ ድጋፍ እየተደረገ እንዳለ የጉራፈርዳ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።
ሞሚና የከብት እርባታ ስራ ማህበር በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ኩጃ ከተማ በወተት ሀብት ልማት ስራ ዘርፍ የተሰማራ ማህበር ሲሆን ማህበሩ ከተመሰረተ ከአንድ አመት በላይ ማስቆጠሩን የማህበሩ ባለቤት ወይዘሮ ሞሚና ጀማል ተናግረዋል።
ማህበሩ አሁን ላይ 11 የሚሆኑ የውጭ ዝርያ ያላቸው ከብቶች ያሉት ሲሆን የወተት ምርትን በኩጃ ከተማና አካባቢው ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ማህበሩ ከሁለት ከብቶች ብቻ በቀን ከ50 ሊትር በላይ ወተት እያገኙ መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሞሚና 9 ላሞች ነፍሰጡር እንደሆኑም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከሁሉም ላሞች ከ200 ሊትር በላይ የወተት ምርት በቀን እያቀረቡ እንደነበር የጠቆሙት ባለቤቷ፥ ያጋጥማቸው የነበረው የገበያ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀረፍ መቻሉን አንስተዋል።
ማህበሩ ወደስራ ከገባ ጀምሮ በአከባቢው ለሚገኙ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድሎች መፍጠር መቻሉን ወይዘሮ ሞሚና ተናግረዋል።
በአካባቢው በበጋ ወቅት ያለው የውሀ ዕጥረት ለእርባታ ስራው ችግር ከመሆኑ ባለፈ የወረዳው መንግስት ድጋፍና ዕገዛ ግን ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ማህበሩ ከ5 ሚሊዮን ብር ካፒታል በመያዝ ወደ ስራ የገባ ሲሆን በቀጣይም ስራውን ይበልጥ በማስፋፋት የማቀነባበሪያ ማዕከል ለመገንባት ግብ ይዘው እየሰሩ እንዳሉ ወይዘሮ ሞሚና ተናግረዋል።
የጉራፈርዳ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር ዳዊት ወልደሰንበት እንደተናገሩት በወረዳው በርካታ የእንስሳት ሀብት መኖሩን ጠቁመው ማህበረሰቡን ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በኩጃ ከተማ በዘመናዊ የከብት እርባታ ስራ የተሰማራው ማህበሩ በከተማዋ የህብረተሰቡን የወተት ፍላጎት ለመመለስ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።
ማህበሩን ውጤታማ እንዲሆን ሙያዊ ድጋፍና ዕገዛ በቅርበት ከመስጠት ባለፈ ከሚዛን እንስሳት ጤና ጥበቃ ላብራቶሪ ማዕከል ጋር በመቀናጀት በየጊዜው ክትትልና ክትባት እየተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሚዛን እንስሳት ጤና ጥበቃ ላብራቶሪ ማዕከል ባለሙያዎች በጉራፈርዳ ወረዳ ኩጃ ከተማ የሚገኘውን የከብት እርባታ ማህበር የስራ እንቅስቃሴውን ተዘዋውረው በመመልከት ሙያዊ ድጋፎችን አድርገዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሪጅን በሚዛን ዲስትሪክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው 9ኛው የምስለ ችሎት ውድድር በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ