አስፈጻሚው አካል የህብረተሰቡን ጥያቄ ወደ እቅድ በመቀየር የህዝብ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ተገለጸ
ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች አስፈጻሚው አካል ወደ እቅድ በመቀየር የህዝብ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ በሚችል መንገድ ማከናወን እንዳለበት በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመን መፍጠር ለችግሮች መፍትሄ ለማበጀት እንደሚረዳና የህብረተሰቡን ሰላምና ልማት ለማሳደግ እንደሚያስችል በምክር ቤቱ የህዝብ መድረክ የተሳተፉ የከተማዉ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፈሰሰወርቅ ገብረሰንበት በምክር ቤቱ የ2017 በጀት አመት የህዝብ መድረክ በተካሄደበት ወቅት እነደገለጹት፥ የውይይት መድረኩ በበጀት አመቱ አስፈጻሚው ሲያከናውናቸው በነበሩ ተግባራቶች ላይ በልማት፣ በፍትህ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰላምና ጸጥታ ዙርያ የህዝቡን ጥያቄና ሃሳብ ለመረዳት ያለመ ነው፡፡
በቀጣይም ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች አስፈጻሚው ወደ እቅድ በመቀየር ህብረተሰቡን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመው፥ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት በዋናነት በመሰረተ ልማት፣ በኑሮ ውድነት፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ በሰላምና በጸጥታ ችግሮች እንደሚነሱ ተናግረዋል፡፡
አስፈጻሚው አካልም ችግሮቹን በመለየት በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የእቅድ አካል አድርጎ መፍታት እንዳለበት የተናገሩት ወ/ሮ ፈሰሰወርቅ፥ የህዝቡን ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ በሚችል መንገድ መከናወን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ከከተማዉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሰይፉ ወልዴ፣ አቶ ብርሃኑ ገብሬና ወ/ሮ ይመኙሻል ደመላሽ መድረኩ መዘጋጀቱ በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመን በመፍጠር ለችግሮች መፍትሄ ለማበጀት እንደሚረዳና የህብረተሰቡ ሰላምና ልማት ለማሳደግ እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
በከተማው ለሚነሱ የኑሮ ውድነት፣ የሰላም፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲፈቱ የጠየቁት ነዋሪዎቹ፥ የህብረተሰቡን የሰላም እሴት ማጠናከር እንደሚገባና የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት የተሻለ ቢሆንም ፍትሃዊ ስርጭትን ማሳደግ እና የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት እንዳለበትና የከተማ ግብርናን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሰንበት ገበያንና ሸማቾች ማህበራትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው፥ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ተጀምረው ያልተጠናቀቁና ጥገና የሚያስፈልጋቸው መንገዶች መገንባትና የከተማዉ ጽዳትና ዉበት መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አስቻለው ገብሬ የህዝብ መድረክ መዘጋጀቱ ጠንካራና ደካማ ጎን ለመለየት እንደሚረዳ ጠቁመው በቀጣይ የእቅድ አካል ተደርጎ ለመስራት እንደሚያግዝ ተናግረዋል ፡፡
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ቶፊቅ ሱልጣን በበኩላቸው፥ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች የልማት ፍላጎቶች ለመሙላትና በቀጣይ ስራዎች ለማካተት እንደሚረዳ ገልጸዉ፥ የመንገድ ከፈታ፣ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የቦይ ከፈታና ጥገና እና በሌሎችም ጉዳዮች መፍትሄ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሂደት ላይ ያሉ ተግባራትን ለማስቀጠል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን እገዛ ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዉ እየተገባደደ ባለው በጀት አመት የተጀመሩትን በማጠናቀቅና ሌሎች የተነሱ ጉዳዮች የቀጣይ አመት እቅድ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ: ኄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሪጅን በሚዛን ዲስትሪክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው 9ኛው የምስለ ችሎት ውድድር በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ