የኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከሉ ረገድ የማህበራት አደረጃጀቶች አይተኬ ሚና መጫወታቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
የክልሉ ጤና ቢሮ በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ በማህበር ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ ማህበራት፣ ወጣቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ውይይት በጂንካ ከተማ አካሂደዋል።
አሰተያየታቸውን ከሰጡን መካከል በደቡብ ኣሪ ወረዳ የኮከብ ኤች አይ ቪ በደማቸው ያሉ ወገኖች ማህበር ሰብሳቢ ወ/ሮ አፀደ አድነው፤ ኤች አይ ቪ በኛ ይብቃ በማለት በማንኛውም ቦታ በማስተማር ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም በመንግስት በኩል የሚደረጉ ድጋፎችና ማነቃቃቶች ብሎም ለማህበራት የሚደረጉ ድጋፎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አንሰተው፤ ኤች አይ ቪ አምራች ኃይልን የሚያሳጣ በመሆኑ ወጣቱም ሆነ ማንኛውም ሰው የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ በመተግበር ያለ ፍርሃት ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል መክረዋል።
ሌላኛው የጋርዱላ ዞን ዳግም ህይወት ኤች አይ ቪ በደማቸው ያሉ ወገኖች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ከኖ ከዳ፤ አሁን ላይ የስርጭት ምጣኔው እየጨመረ መሆኑንና ይህንን ለመከላከል መድረኩ ግንዛቤያቸውን ይበልጥ ያሰፋ እንደሆነ ገልፀዋል።
የኣሪ ዞን ኤች አይ ቪ ኤድስ አሰተባባሪ አቶ ፍርዱ ለማ እና የጋሞ ዞን ኤች አይ ቪ ኤድስ አሰተባባሪ አቶ ዚሎ ዚዳ፤ ይህ መድረክ በኤች አይ ቪ ኤድስ ያለውን መዘናጋትና የግንዛቤ ክፍተት በማረም የስርጭት ምጣኔውን ለመቀነስ ከንቅናቄ ጀምሮ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው መድረኩ ተግባሩን በማነቃቃት አደረጃጀቶችን በማጠናከር ለጋራ ውጤት እንዲመጣ ያስችላል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማትዮስ ጋርሾ፤ በአጠቃላይ የመድረኩ አላማ እየጨመረ ያለውን የኤች አይ ቪ በሽታ ለመከላከል እና አደረጃጀቶችን በማጠናከር ቦርድ አቋቁሞ በመስራት በዘርፉ ያሉ ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነው ብለዋል።
በእስከዛሬው ተግባር በኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከሉ ዙሪያ የማህበራት አደረጃጀቶቹ አይተኬ ሚና መጫወታቸውን ያነሱት ኃላፊው፤ በዚህም ከ1 በመቶ በታች እንዲሆን አስችለዋል ብለዋል።
በቀጣይ ከግንዛቤ ሥራዎች ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችን በማረም በአጠቃላይ ጤናማ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠርም ያለመ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
በውይይቱ መነሻ ሰነድ ቀርቦ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶች ተነስተው በመድረኩ መሪ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በሚዛን አማን ከተማ አረንጓዴ አሻራ አሳረፉ
የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ነው
በክልሉ በተያዘው የበልግ ወቅት በኩታገጠም ሩዝና በቆሎ እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች ተስፋ ሰጪ የሆነ የምርት ውጤት እንድናይ አስችሎናል አሉ።