በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ወቅትን መነሻ አድርገው የሚከሰቱ የእንስሳት በሽታዎችን ፈጥኖ ለመከላከል የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሚዛን እንስሳት ጤና ጥበቃ ላብራቶሪ ማዕከል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ወቅትን መነሻ አድርገው የሚከሰቱ የእንስሳት በሽታዎችን ፈጥኖ ለመከላከል የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ማዕከሉ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የእንስሳት በሽታዎች ቅኝትና አሰሳ አካሂዷል።
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ በአፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት በቀዳሚነት የምትጠቀስ ቢሆንም፥ ከእንስሳት ሀብቱ ተገቢውን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች።
ታዲያ ለችግር ምክንያት ተብሎ ከሚጠቀሱት ደግሞ እንስሳትን የሚያጠቁ የተለያዩ በሽታዎች መኖራቸው በዋናነት እንደሚጠቀስ የዘርፉ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
የሚዛን እንስሳት ጤና ጥበቃ ላብራቶሪ ማዕከል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ወቅትን መነሻ አድርገው የሚከሰቱ የእንስሳት በሽታዎችን ፈጥኖ ለመከላከል የሚያስችሉ የተጠናከረ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን በማዕከሉ የእንስሳት በሽታ ቅኝት ኦፊሰርና የደስታ መሰል የበጎችና የፍየሎች በሽታ መከላከል ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ዳዊት ደጀኔ ተናግረዋል።
ማዕከሉ በቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ኩጃ ከተማ ተገኝተው የበግና ፍየል እርባታ ስራ ከሚሰሩ የተመረጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በእንስሳት በሽታዎች ዙሪያ የቅኝትና አሰሳ ስራ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የደስታ መሰል የበግና ፍየሎች በሽታ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ከሚታወቁት የእንስሳት በሽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዳዊት፥ በሽታው እጅግ በጣም ተላላፊና ገዳይነት ያለው አደገኛ በሽታ በመሆኑ የበሽታው ቅኝትና አሰሳ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የማዕከሉ የላብራቶሪ ባለሙያ ወይዘሮ የምስራች ሳሙኤል በደስታ መሰል የበግና ፍየሎች በሽታ እንስሳቱ ሲጠቁ የሚያሳያቸው ምልክቶችን በተመለከተ ለህብረተሰቡ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሽታው በእንስሳቱ ላይ ሲከሰት በዓይንና አፍንጫ ፈሳሽ፣ አፍ አካባቢ መቁሰል፣ ከፍተኛ የሆነ ሽታ ያለው ተቅማጥ በዋናነት እንደሚያሳዩ ገልጸዋል።
የጉራፈርዳ ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት የእንስሳትና አሳ ሀብት ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር ዳዊት ወልደሰንበት በበኩላቸው በወረዳው የሚገኙ አርሶአደሮች ከሰብል ልማት ጎን ለጎን የእንስሳት እርባታ ስራ መተዳደሪያቸው መሆኑን አንስተዋል።
በወረዳው ባለፉት አመታት የደስታ መሰል የበግና ፍየሎች በሽታ ተከስቶ እንደነበር የተናገሩት ባለሙያው ከ22ሺህ በላይ በግና ፍየሎች ክትባት በመስጠት መከላከል ተችሏል ብለዋል።
ከላብራቶሪ ማዕከሉ ጋር በመቀናጀት በቅርቡ ባደረጉት ቅኝት የበሽታው ምልክቶች መታየታቸውን የተናገሩት ዶክተር ዳዊት ዳግም በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል የክትባት ዘመቻ በቅርቡ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
የማዕከሉ ባለሙያዎች በጉራፈርዳ ወረዳ ኩጃ ከተማ በነበራቸው ቆይታ በከተማዋ የሚገኘውን የሞሚና ዘመናዊ የከብት እርባታ ማዕከል የስራ እንቅስቃሴውን በመመልከት ሙያዊ ድጋፎችን አድርገዋል።
ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በሚዛን አማን ከተማ አረንጓዴ አሻራ አሳረፉ
የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ነው
በክልሉ በተያዘው የበልግ ወቅት በኩታገጠም ሩዝና በቆሎ እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች ተስፋ ሰጪ የሆነ የምርት ውጤት እንድናይ አስችሎናል አሉ።