ለፍትህ ሥርዓት ውጤታማነት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
ዩኒቨርሲቲው ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ሥራን ለማሳለጥ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የነፃ ህግ ድጋፍ አገልግሎት ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብር ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ፤ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ዶክተር ተክሉ አክለውም በፍትህ ዘርፍ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ከእነዚህም መካከል ነፃ የሕግ አገልግሎት እና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ የትምህርት ቤት መምህርና የማህበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ ጌትነት ደባልቄ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በ25 ማዕከላት የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት በአካባቢው ተደራሽነታቸውን ለማረጋገጥ አዲስ 10 የሕግ ማዕከላት እንደሚከፈቱ መምህር ጌትነት አስረድተዋል።
ይህ የ16 ወራት ፕሮጀክት ዓላማው በዋናነት በወንጀል ጉዳዮች ዙሪያ የነፃ የሕግ አገልግሎትን ተደራሽነት ማሻሻል ነው ተብሏል።
ፕሮጀክቱ አዳዲስ የሕግ ማዕከላትን ከመክፈት በተጨማሪ በማረሚያ ተቋማት ውስጥም አገልግሎት ለማስፋፋት እንዲሁም ቀደም ሲል የነበሩትን ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎቶችን ለመደገፍ እና በሕብረተሰቡ ውስጥ ግንዛቤን ለማሳደግ ያለመ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 14 ዓመታት ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን መምህር ጌትነት ገልፀው፤ ለዚህ ፕሮጀክትም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመድኃኒት እና የወንጀል ጽ/ቤት የተገኘ 10 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል ብለዋል።
በመድረኩ የወንጀል ፍትህ ሥርዓት በኢትዮጵያ እና የህግ ማዕቀፍ በሚል ርዕስ የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህር ጆርጅ አላሶ አቅርበዋል። በዚህም በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ያላቸው መብትና የሰብዓዊነት አያያዙ ዙሪያ ሰፊ ገለፃ ተደርጓል።
በመጨረሻም የተለያዩ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥቶባቸዋል።
ዘጋቢ፡ አማሮ አርሳባ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሪጅን በሚዛን ዲስትሪክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው 9ኛው የምስለ ችሎት ውድድር በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ