በቱሪዝም ረገድ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚገባና ሀብታችንንና ጸጋዎቻችንን ለማስተዋወቅ ዲጂታል ሚዲያውን ይበልጥ መጠቀም እንደሚያስፈልግ የኤፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ
”የቱሪዝም ሀብቶችን ለዘላቂ ሠላምና ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል ከባለድርሻ አካላትና ከመሪ ተዋንያን ጋር የቱሪዝም ትውውቅ የፓናል ውይይት በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ተደርጓል፡፡
የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ በክልሉ ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ባህልና እሴቶች መኖራቸውንና እነዚህን በማስተዋወቁና ጠብቆ ከማቆየት አኳያ ሰፊ ስራ ይጠይቃል።
እንዲሁም በየአካባቢው የሚታዩና ለዘርፉ እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍታት ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ ባሻገር ፓርኮችና ሌሎች ብዝሀ ህይወቶች በአግባቡ ተጠብቀው እንዲቆዩ ከፍተኛ ጥበቃ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ወይኒቱ መልኩ፤ በክልሉ ያሉትን ሀብቶች ማስተዋወቅና ሰደድ እሳት፣ ህገወጥ አደንና መሠል ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚገባና የክልሉ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ዶ/ር ቦሻ ቦምቤ፤ በክልሉ ያሉ ባህላዊ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩና የኢኮኖሚ አቅሙን እንዲያሳድጉ የክልሉ መንግስት ይበልጥ ያግዛል ብለዋል።
የኢፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ፤ የክልሉን ባህል ታሪክ ቅርስ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መስህቦችን ከመጎብኘት አንጻር ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን በሰፊው መጋበዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በቱሪዝም ረገድ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ የሚገልጹት ሚኒስትሯ፤ ሀብታችንንና ጸጋዎቻችንን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ዲጂታል ሚዲያውን መጠቀም ይገባናል ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ላይ አጥጋቢ ስራዎች የመኖራቸውን ያህል ሊሻሻሉ የሚገባቸው የመሠረተ ልማትና መሰል ውስንነቶች በመኖራቸው በየደረጃው ትኩረት ሊደረግባቸው እንደሚገባ ጠቅሰዋል ሚኒስትሯ።
በቀጣይ እንደ ሚኒስቴር መ/ቤት አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ሁሉ ክልሉን እንደሚደግፉና እንደሚያግዙ አበክረው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሪጅን በሚዛን ዲስትሪክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የህግ ትምህርት ቤቶች መካከል የተካሄደው 9ኛው የምስለ ችሎት ውድድር በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ተጠናቀቀ