በኬሚካል ሳርን በማክሸፍና መሬትን በመሰንጠቅ ብቻ ዘርን የመዝራት አዲስ ቴክኖሎጂን በወረዳው 4 ቀበሌያት በ11 ሔክታር መሬት ላይ የመሞከር ተግባር መከናወኑም ተጠቁሟል።
በወረዳው ቃቆ ቡነከር ቀበሌ በእርሻ ማሳቸው ላይ ያገኘናቸው አርሶና ከፊል አርብቶ አደር ዳዮ ፓኮ፣ ዱሞ ዱመላክ እና ወ/ሮ ጎይቲ ኡርመኒ እንደተናገሩት፤ በበልጉ እርሻ አስቀድመው በማረስ በቆሎ ማሽላ እና አደንጓሬ ሰብሎችን በመዝራት አሁን ላይ ለአረም በመድረሱ በአረም ተግባር ላይ ይገኛሉ።
ግብአት በመጠቀማቸውና የባለሙያዎችን ምክር እየተቀበሉ በመተግበራቸው ቡቃያውን ብቻ በማየት መርካታቸውንና ቀድሞ ከመኸሩ ባገኙት ምርትም የምግብ ፍጆታቸውን ከመቻል በተጨማሪ ገበያ በማቅረብና በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቡነከር ቀበሌ ሰብል ልማት ባለሙያ ወ/ሪት ፍሬህይወት አሸብር እንደገለጹት፤ በቀበሌው የሚገኘው አርሶና ከፊል አርብቶ አደር በበልጉ እርሻ የተለያዩ ሰብሎችን አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የግብአት ተጠቃሚ እንዲሆን የማመቻቸትና የመደገፍ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
በበልጉ እርሻም አጠቃላይ በቀበሌው ከ1 ሺህ 7 መቶ በላይ ሔክታር መሬት በበቆሎ፣ ማሽላና አደንጓሬ እንዲሁም የጓሮ አትክልቶች መሸፈኑን አስረድተዋል።
በ2017 የበልግ እርሻ አጠቃላይ በወረዳው በሚገኙ 34 የከተማና ገጠር ቀበሌያት ከ27 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በቆሎ ማሽላ፣ ጤፍና ሰሊጥ እንዲሁም በጓሮ አትክልቶች ለማልማት ታቅዶ ከ25 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በማረስ ከ23 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የገለጹት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ክላሽ አንግሪ ናቸው።
በወረዳውም አጠቃላይ በበልጉ እርሻ ከተዘራው መሬት ከ4 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት በተጓደለ እና ሙሉ ፓኬጅ ሲሆን ከ19 ሺህ ሔክታር በላይ ያለ ቴክኖሎጅ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው በዚህም በሁሉም ቀበሌያት ከ49 ሺህ በላይ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አዲስ ቴክኖሎጅ የሆነውን በእርሻ መሬት ላይ ሳርን በኬሚካል በማክሸፍ መሬቱን በመሰንጠቅ ብቻ ዘርን የመዝራት ቴክኖሎጅን ከሀይለማርያም እና ሮማን ፋወንዴሽን ጋር በመተባበር በቃቆቡነከር፣ ጎልድያ፣ ሉቃ እና ኦልካ ኪቦ ቀበሌያት በ20 አርሶ አደሮች ማሳ በ11 ሔክታር መሬት ላይ ሙከራ በመዝራት ቡቃያው ተስፋ ሰጭ ውጤት መታየቱን አቶ ክላሽ ተናግረዋል።
ለዚህ ተግባርም ሀየለማርያምና ሮማን ፋወንዴሽን የኬምካል፣ የምርጥ ዘርና የግብአት አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በመሸፈኑ ምስጋና አቅርበው ውጤቱ ታይቶ ተሞክሮውን ወደ ሌሎች ቀበሌያት የማስፋት ተግባር እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።
አጠቃላይ በበልጉ እርሻ ከለማው ከ25 ሺህ ሔክታር በላይ መሬትም በምርት ዘመኑ ማጠቃለያ ከ903 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከማብራሪያው ለመገንዘብ ተችሏል።
ዘጋቢ፡ ተመስገን ሰይፉ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በክልሉ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን በሚዛን አማን ከተማ አረንጓዴ አሻራ አሳረፉ
የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት 5ኛ አመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች እየተከበረ ነው
በክልሉ በተያዘው የበልግ ወቅት በኩታገጠም ሩዝና በቆሎ እያለሙ ያሉ አርሶአደሮች ተስፋ ሰጪ የሆነ የምርት ውጤት እንድናይ አስችሎናል አሉ።