ሀዋሳ: ሚያዝያ 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የከተማዋ ማህበረሰብ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት አንዳለበት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃለፊ አቶ ታደለ በቀለ ገለፁ።
የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተከናወነ የፅዳት ዘመቻ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የከተማ አስተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃለፊ አቶ ታደለ በቀለ እንዳሉት የከተማዋ ማህበረሰብ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት አለበት።
ከተለያዩ ቤተ እምነት የመጡ ወጣቶች በዚህ ተግባር መሳተፋቸው ማህበረሰቡ አካባቢውን ማፅዳት ባህል እንዲያደርግ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የወልቂጤ ከተማ አሰተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አልዩ ናስር በበኩላቸው በከተማው እየተከናወነ ያለው የፅዳት ዘመቻ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የምናሳይበት፣ አንድነታችንን የምናጠናክርበት በጋራ ከተማችንን ፅዱና ውብ አድርገን የምንይዝበት ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በከተማው የኮሪዳር ልማት በፍጥነት እየተከናወነ በመሆኑ ህብረተሰቡ የፍሳሽ ቆሻሻ አከባቢውን እንዳያበላሽ በየሰፈሩ በጽዳት ዘመቻ ስራ ላይ መጠናከር እንደለበት አቶ አልዩ ጠቁመዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጀት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ቶፊቅ ሱልጠን በበኩላቸው ወልቂጤን በየሳምንቱ የከተማው አመራር ፣ ነዋሪዎች በጋራ በመሆን እያጸዱ እንደሆነ ገልጸው በነገው እለት የሚከበረውን የትንሳኤ በአልን ምክንያት በማድረግ በመናኸሪያው ዙሪያ በህብረት ወጥተው እያጸዱ እንደሆነ ገልጸዋል ።
በተለይም ከተማ አስተዳደሩ የቆሻሻ አወጋገድ ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ በመስራት ከተማውን ለቱሪስትና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንድትሆን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ቶፊቅ፥ በተለይም ሰሞኑ ከበኣል ጋር ተያይዞ እርድ ስናከናውን የተረፉ ምርቶች በተዘጋጀ ቦታ በማስቀመጥና ማዘጋጀት ቤቱ ያሰማራቸው ሰራተኞ በየሰፈሩ ዞረው ስለሚያነሱ ቆሻሻውን በተገቢው በማስወገድ ረገድ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድረሻ መወጣት እንደለበት ጠቁመዋል።
አክለውም ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ማራኪ ለማድረግ በሚከናወነው ተግባር ላይ በአከባቢው ቆሻሻን የሚጠየፍ ትውልድ ለማፍራት የሚተገበሩ ስራዎች በቀጣይም በበጎ ስራዎች ላይ ተጠናክሮ መቀጠል እንደለባቸው ስራአስኪያጁ አሳሰበዋል።
የወልቂጤ ከተማ ቃላ ህይወት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ዘርፍ ሃለፊና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር አስፋው ኦጭሶ በበኩላቸው ነገ በአደባባይ ለሚከበረው ለትንሳኤ በአል አስቀድሞ ከተማው የበለጠ ውብ መሆን ስላለበት ከከተማው ወጣቶች በጋራ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል
በሌላ በኩል ደግሞ ለህብረተሰቡ፣ አብሮነትን፣ መቻቻልን ፣ፍቅርን አንድነትን ፣እንዲሁም በከተማው ልማት ላይ ቁርጠኝነት ለማሳየት በህብረት እየሰሩ እንደሆነ ፓስተር አስፋው አብራርተዋል
በፅዳት መርሀ -ግብሩ ላይ ያገኘናቸው ወጣቶች በሰጡት አስተያየት በጎ መስራት በየትኛውም ሀይማኖት የሚደገፍና ከፈጣሪ ዘንድ የተወደደ ተግባር በመሆኑ በመሳተፋቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በቀጣይም በከተማው በሚኖሩ በተለያዩ በጎ አገልግሎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸው ወጣቶቹ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ በደጋጋ ሂሳቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ