መጋቢት 24 በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ የፖለቲካ እጥፋት የተደረገበት ነው – ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) መጋቢት 24 በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ የፖለቲካ እጥፋት የተደረገበት መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ ገለጹ፡፡
ትናንት፣ ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና በሚል መሪ ቃል የመጋቢት 24 ቀን በዓል በፓናል ውይይት በአርባምንጭ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ስራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ፤ መጋቢት 24 በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ የፖለቲካ እጥፋት የተደረገበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ መንግስታት ለረጅም አመታት ሰልጣን በመያዝ በጠመንጃ የመምራት እና በሃይል የመግዛት ልምድ የተቀለበሰበት በመሆኑ በፖለቲካው የመጣው ለውጥ ቀላል እንዳልሆነ ዶ/ር አበባየሁ ገልፀዋል።
ግብርናው ያልዘመነና የሀገሪቱን ህዝብ መመገብ ያልቻለ እንደነበረ ገልፀው፤ ከለውጡ ወዲህ ትኩረት በመሰጠቱ በእርዳታ ይገባ የነበረውን ስንዴ ሀገር ውስጥ በማምረት የውጪ ምንዛሪን ያስቀረ 7 የለውጥ አመታትን አስቆጥረናል ነው ያሉት።
የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር ደምስ አድማሱ፤ የለውጡ መንግስት ተግዳሮቶችን በማለፍ ከጫፍ እስከ ጫፍ በማስተሳሰርና በአንድነት ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን አስረድተዋል።
ሰፋፊ መሬቶች ለእርሻ እንዲውሉ በማድረግ፣ የውጪ ምንዛሪን በማስቀረት፣ ለጎረቤት ሀገራት የተረፍንበትና የህዝቦች የልማት ጥያቄ ምላሽ ያገኘው በለውጡ መንግስት እንደሆነ ገልፀዋል።
በመፍጠንና መፍጠር እሳቤ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የገለፁት ዶ/ር ደምስ የ7 ዓመት ድሎች ላይ ቆመን ነገን የተሻለ ለማድረግ እንተጋለን ብለዋል።
በመድረኩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር መስፍን መንዛ፤ መጋቢት 24 በለውጡ መንግስት እንደ ሀገር የተመዘገቡ ለውጦችን የምንዘክርበትና አዲስ ምእራፍ የምንጀምርበት መሆኑን አስታውቀዋል።
አክለውም ቅቡልነት ያለው ሀገረመንግስት ለመገንባት እድል የሰጠ እና ነፃና ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋም የገነባ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በመድረኩም በምሁራን የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ገነት መኮንን – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በሀገሪቷ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ
ድልና ውጤት የሚመጣው በምኞት ሳይሆን ጠንክሮ በጋራ መሥራት ሲቻል ነው ሲሉ ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ ተናገሩ
የመጋቢት ፍሬዎች ትናንት፣ ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና በሚል መሪ ቃል በማረቆ ልዩ ወረዳ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው