“መጋቢት ሀገራችን ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ የታደገ ወር ነው ” – አቶ ኡስማን ሱሩር
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዱራሜ ክላስተር ከፍተኛ አመራሮች እና በከምባታ ዞን በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች “ትላንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ቃል የለውጡ አመት የጀመረበትን መጋቢት 24 ሰባተኛ ዓመትን በተለያዩ ሁነቶች እያከበሩ ይገኛሉ።
በመርሃግብሩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንዲሁም የክልሉ የገጠር ክላስተር ከፍተኛ አመራሮችና የከምባታ ዞን የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የለውጥ ጊዜያት የተከናወኑ ስራዎች የታሰቡ ሀገራዊ ትልሞችን ያሳካና ቀጣይም የሚያሳካ መሆኑን የተናገሩት የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ፤ በእነዚህም ዓመታት በርካታ የልማት ትሩፋት የተገኙበት መሆኑን አንስተዋል።
የለውጡ ዓመታት ለኢትዮጵያውያን ብዙ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ያነሱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር፤ በዚህም በርካታ ፈተናዎች በድል የተቀየሩበት መሆኑንም ገልፀዋል።
መጋቢት ሀገራችን ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ የታደገ፣ የዘመናት የመገፋፋትና የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህላችንን ቀይሮ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንዲሁም የበለፀገችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ የማሻገር ህልም የሰነቀ በታላላቅ ስኬቶች የታጀበ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ዕውን የሆነበት ታሪካዊ ወር መሆኑን አንስተዋል።
የመጣውን ውጤት በጋራ በመስራት ልናዘልቀው ይገባል ሲሉም አቶ ኡስማን ተናግረዋል።
በመድረኩ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተገኙ ውጤቶችንና ፈተናዎችን የሚዳስሱ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ቃለአብ ጸጋዬ

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ