ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ወደ ግማሽ ፍፃሜ አለፉ
በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ የተሳተፉት ሶስቱም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል።
ዛሬ ማለዳ በቻይና ናንጂንግ መካሄድ በጀመረው 20ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ነው አትሌቶቹ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያለፉት።
በምድብ 1 የተሳተፈችው አትሌት ሀብታም ዓለሙ 2 ደቂቃ ከ04 ከ48 ማይክሮ ሴኮንድ በሆነ ሰዓት 3ኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሻግራለች።
በ2ኛው ምድብ የተካፈለችው የወቅቱ የርቀቱ አሸናፊ አትሌት ፅጌ ድጉማ 2 ደቂቃ ከ04 ሴኮንድ ከ52 ማይክሮሴኮንድ ምድቧን በበላይነት አጠናቃ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።
በ3ኛው ምድብ የተወዳደረችው አትሌት ንግስት ጌታቸው 2 ደቂቃ ከ03 ሴኮንድ ከ91 ማይክሮሴኮንድ የግሏን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅላለች።
የሴቶች 800 ሜትር የግማሽ ፍፃሜ ውድድር በነገው ዕለት ከማለዳው 1 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ጀምሮ የሚካሄድ ይሆናል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉበት ውድድሮች ዛሬ ከሰዓት በኋላ ሲካሄዱ በሁለቱም ፆታ 1500 ሜትር ግማሽ ፍፃሜ ውድድር ይደረጋል።
በዚህም መሰረት ከቀኑ 7:33 ላይ የሴቶች 1500 ሜትር ግማሽ ፍፃሜ ይካሄዳል።
በግማሽ ፍፃሜው ምድብ 1 አትሌት ጉዳፍ ፀጋዬ፣ በምድብ 2 አትሌት ወርቅነሽ መሰለ እና በምድብ 3 አትሌት ድርቤ ወልተጂ ወደ ፍፃሜው ለማለፍ ይፋለማሉ።
የወንዶች 1500 ሜትር ግማሽ ፍፃሜ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ18 ላይ ሲካሄድ በምድብ 5 የኢትዮጵያው ተወካይ አትሌት መለሰ ንብረት ይካፈላል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 6ለ1 አሸነፈ
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ የምስክር ወረቀት ተሰጠው
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ከአፍሪካ 1ኛ ከዓለም 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች