ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የወላጆችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር ይገባል
ሀዋሳ፣መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል የወላጆችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ የቀድሞ የቆሻ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለትምህርት ቤቱ 350 በላይ የተለያዩ አጋዥ መጽሐፍትን ድጋፍ አድርገዋል።
የቆሻ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት አስተባባሪ ታረቀኝ አስፋው እንደገለጹት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባባር ለመጀመሪያ ዙር ከ130ሺ ብር በላይ በማሰባሰብ ከ350 በላይ የተለያዩ መጽሐፍት ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
ዋና ዓላማው በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ውጤት መቀነስ መነሻ በማድረግ የተማሪዎችን ውጤት ለመሻሻል የአጋዥ መጽሐፍት ድጋፍ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ከድጋፉ ባሻገር የትምህርት ፍላጎት ማነስና ውጤት ለመቀነስ መሠረታዊ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ጥናት በማካሄድ ከአከባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት መደረጉንም አቶ ታረቀኝ ጠቁመዋል።
በሶሮ ወረዳ የቆሻ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ወ/ሪት መሰረት ያዕቆብ የቀድሞ ተማሪዎች ያደረጉት ጉብኝትና ድጋፍ በተማሪ ውጤት ላይ ያለው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ነው ብለዋል::
የቀድሞ ተማሪዎች ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ሌሎችም መሰል ድጋፎችን እንዲያደርጉ ወ/ሪት መሰረት ጠይቀዋል።
የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች በበኩላቸው በተደረገው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው፣መጽሐፍቶቹ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመላክተዋል::
በወቅቱ የተገኙት የሶሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ኤርገኖ በበኩላቸው የቀድሞ ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ያልተሟሉ ግብዓቶችን ለማሟላት ያደረጉት አስተዋፅኦ የጎለ ነው ብለዋል::
በትምህርት ቤቱ የታየውን የተማሪዎችን የውጤት ስብራት ለመጠገን በቆሻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጀመሩ ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት ቤት ውሎ በመከታተል አጋዥ ሊሆኑ እንደሚገባም አቶ ብርሃኑ አሳስበዋል ።
በመርሃ-ግብሩ የቀድሞ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መላው የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:-በየነ ሰላሙ ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የግብርናን ምርትና ምርታማነት ማዘመንና ማሳደግ ዘላቂ ልማትን እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑ ተጠቆመ
ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ