ህፃናት በወቅቱ ተገቢውን ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ንቁና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ የሚያግዝ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ መጋቢት 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህፃናት በወቅቱ ተገቢውን ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ንቁና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ የሚያግዝ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ::
በክልሉ ለ10 ተከታታይ ቀናት እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ላልተከተቡ እና ክትባት ጀምረው ላቋረጡ ህፃናት ቤት ለቤት ዘመቻ በማካሄድ ክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ በኪዲጊሳ ቀበሌ ተካሂዷል።
ህፃናት በወቅቱ ተገቢውን ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል፣ ንቁና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ የሚያግዝ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ገልጸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ባደረገው ጥናት መሠረት ክትባት ያልተከተቡ እና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት በክልሉ መኖራቸዉ በተረጋገጠባቸዉ አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ በዘመቻ መልክ ለተከታታይ አስር ቀናት የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
በየወቅቱ የሚሰጡ ክትባቶች የህፃናትን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉንም አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል::
ክትባት ባለመወሰዱ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለመከላከል ህፃናት ክትባት በተገቢው እንዲወስዱ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል::
ባለፉት ጊዜያት በክልሉ በዘመቻ መልክ በተሰራው ስራ 21 ሺህ ህፃናት ክትባት ያልተከተቡና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ መኖራቸውን በመረጋገጡ ደግም ክትባት እየተሰጠ እንደሆነ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አመላክተዋል::
በክልሉ በአንድ ልዩ ወረዳ የታየው የኩፍኝ በሽታ መከሰት ምክንያት ያልተከተቡ ህፃናት መኖራቸውን የሚያሳይ እንደሆነ አቶ አሸናፊ ጠቅሰዋል::
የክትባት አሰጣጥ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም አቶ አሸናፊ ጥሪ አቅርበዋል።
በሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶችና ህፃናት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሻለ መኔቦ እንደገለጹት፤ ክትባት ያልተከተቡና ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባቸዋል።
በዞኑ የክልሉ ጤና ቢሮና ዩኒሴፍ ባደረጉት ድጋፍ መሠረት ክትባት ያልተከተቡ እና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ህፃናት መኖራቸዉ በተረጋገጠባቸዉ 5 ወረዳዎች በዘመቻ መልክ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አስር ቀናት የሚሰጥ እንደሆነም አቶ ተሻለ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የግብርናን ምርትና ምርታማነት ማዘመንና ማሳደግ ዘላቂ ልማትን እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑ ተጠቆመ
ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ