ሀዋሳ፡ መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሚዛን አማን ከተማ በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስደው ወደስራ ባልገቡ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
እስካሁን መሬቱን ወሰደው ስራ ባልጀመሩ ባለሀብቶች 2 ሄክታር መሬት ተወስዶ ወደ መሬት ባንክ መግባቱም ተመላክቷል።
ከደቡብ ምዕራብ ክልል ብዝኅ ከተሞች ውስጥ አንዷ የሆነችው የሚዛን አማን ከተማ በክልሉ ካሉ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ከተሞች በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናት።
በዞኑ ንግድ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ አዘጋጅነት በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የተገኙት የሚዛን አማን ከተማ ከንቲባ አቶ ግሩም ተማም እንደተናገሩት በከተማዋ በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ 76 የግል ባለሀብቶች መሬት በራሳቸው ይዞታ እና ከከተማ አስተዳደሩ ተረክበው ወደስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ከተማው ካለው ሀብት እና ከሚያመነጨው የገንዘብ መጠን አንጻር ቁጥሩ ውስን ነው ያሉት ከንቲባው የከተማ አስተዳደሩ ለአልሚ ባለሀብቶች ቦታ እያመቻቸ እየሰራ ቢገኝም አንዳንድ ባለሀብቶች ካፒታላቸውን በተገቢው አስመዝግበው ወደስራ ከመግባት አንጻር ጉድለቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በከተማው በክልሉ ውሳኔ አግኝተው በተለያዩ ዘርፎች ወደ ልማት እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ባለሀብቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ከንቲባው አብዛኛዎቹ ወደ ስራ ሲገቡ ባልገቡት ላይ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈም ሁለት ሄክታር ያህል ያለማ የከተማ ቦታ ባለመስራታቸው ወደመሬት ባንክ የገባበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
በከተማም መሬቱን ተቀብለው ወደስራ የገቡ ባለሀብቶችም መክፈል የሚገባቸውን የመሬት ሊዝ ክፍያ በወቅቱ አለመክፈላቸው ተግዳሮቶች መሆናቸውን አንስተው የመክፈል ግዴታዎቻቸውን በተገቢው ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
በከተማው እስከ አንድ ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ በሆቴል እና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች መኖራቸውን ከተማዋ ወደ ፈርጅ አንድ እንድትገባ ያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግሩም በተለይም የተጀመሩ የቺፑድ እና የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በተለያዩ ምክንያቶች በሙሉ አቅም ወደስራ አለመግባታቸው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይ ከባንኮች ብድር አለመመቻቸት፣ በከተማው የኃይል አቅርቦት ችግር መኖር በባለሀብቱ የሚቀርብ ተግዳሮት ይህንን ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተማው መሬት ወስደው አጥረው ወደስራ ሳይገቡ አመታትን ባስቀመጡ አልሚ ባለሀብቶች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ንግድ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኮጁ ባዲካች በበኩላቸው በከተማ በኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት አሰራር ከማለፍ አንጻር ውስንነት መኖሩን ጠቁመው ይህም ችግር መቀረፍ አለበትም ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቴን በበኩላቸው በከተማው መሬት ተረክበው ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶች የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ጠቅሰው ወደስራ ባልገቡት ላይ ያሉ ችግሮች እየተለዩ ወደስራ እንዲገቡ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የግብርናን ምርትና ምርታማነት ማዘመንና ማሳደግ ዘላቂ ልማትን እና የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑ ተጠቆመ
ባለፉት አራት አመታት በክልሉ 270 የውሃ ኘሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ450 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ
ግሎባል ፋይናንስ ባካሄደው የ2025 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የባንኮች ውድድር አዋሽ ባንክ ከ36 የአፍሪካ ምርጥ ባንኮች አንዱ በመሆን እውቅና ማገኘቱ ተገለፀ