በፍየልና በግ ማሞከት ተግባራት ላይ በመሰማራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን በሀዲያ ዞን አንዳንድ የሶሮ ወረዳ ሴቶች ተናገሩ

ህብረተሰቡን በተለያዩ ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት የስራ አጥነት ችግሮችን በዘላቂነት ከመፍታት ባሻገር ራስ አገዝ ኢኮኖሚን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት አስታውቋል።

በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የሸራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሴቶች በኢንተርፕራይዝ በመደራጀት ፍየሎችንና በጎችን በማሞከት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ሴቶቹ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ደስተኞች መሆናቸውን ጠቁመው የመኖና የመድኃኒት አቅርቦት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

አቶ አብርሃም ደካቶ በወረዳው የሸራ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለሙያ ሲሆኑ በአካባቢው በርካታ ተደራጅተው ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን ተሞክሮ በማጋራት ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የወረዳው ሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ከበደ በከተማና የገጠር ቀበሌያት 130 ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ጠቁመው የሴቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በዶሮ እርባታ፣ በግና ፍየል ማሞከትና ሌሎችም ተግባራት የተሰማሩ ሲሆን በዚህም በአካባቢው መደበኛ ያልሆነ የሰዎችን ስደት በማስቀረት በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ የሚሆኑ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አመላክተዋል።

የሶሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ኤርገኖ በበኩላቸው በግልና በኢንተርፕራይዞች በማደራጀት ስራ አጥነትን መቀነስ ብሎም የኢኮኖሚ አቅምን በማጎልበት የምግብ ዋስትናውን ያረጋገጠ ዜጋ መፍጠር የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በወረዳው በዘርፉ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የግብዓቶች አቅርቦት እጥረት ለአብነትም ለበግና ፍየል አርቢዎች የመኖና መድኃኒት አቅሮቦት ችግሮችን ለመፍታት ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በሀገራችን የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር ብሎም የኑሮ ውድነት በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል ዜጎች በመንግስት የተፈጠረላቸውን ምቹ አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን